08/31/2024
ሀዋሳ፤ በማረቆ ሰባት ሰዎች ተገደሉ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ማረቆ ልዩ ወረዳ ማንነትን መሠረት ያደረገ ነው በተባለ ጥቃት አራት የአንድ ቤተሰብ አባላትን ጨምሮ ሰባት ሰዎች መገደላቸው ተሰማ።
*****
ግድያው የተፈጸመው በልዩ ወረዳው ዲዳ ሀሊቦ በተባለ ቀበሌ ውስጥ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የሟቾች የቅርብ ቤተሰብ አባል መሆናቸውን ለዶቼ ቬለ የተናገሩትና አቶ ሁሴን ለመንጎ የተባሉ የዲዳ ሀሊቦ ቀበሌ ነዋሪ ታጣቂዎቹ ጥቃቱን ባለፈው ማክሰኞ የፈጸሙት ሰዎቹ ሌሊት በተኙበት የተኩስ እሩምታ በመክፈት መሆኑን ገልጸዋል።
በጥይት ከተመቱት 11 ሰዎች መካከል የሰባቱ ሕይወት ወዲያ አልፏል። የዐይን አማኙ እንደተናገሩት ከሞቱት መካከል አራቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት ናቸው።
የሟቾቹ ቀብር ትናንት ሐሙስ መከናወኑንም ነው የተናገሩት።
ጥቃቱ ማንነትን መሠረት ያደረገ ፣ ዘግናኝና ታቅዶ በሕጻናትና ሴቶች ላይ የተፈጸመ መሆኑን የጠቀሱት የሟች ቤተሰብ በጥቃቱ የቆሰሉት አራት ሰዎችን ወራቤ ሆስፒታል ማስገባታቸውን መግለጻቸውን ከሀዋሳ ሸዋንግዛው ወጋየሁ በላከው ዘገባ አመልክቷል።
ዶቼ ቬለ ስለጥቃቱ ያነጋገራቸው የማረቆ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጀማል አማሮ በተባለው ቀበሌ ድርጊቱ መፈጸሙን አረጋግጠዋል።
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ አምባሳደር መሾሟ
ኢትዮጵያ ራሷን ራስገዝ አድርጋ በምትቆጥረው ሶማሊላንድ ውስጥ ለሚገኘው ቆንስላ ጽሕፈት ቤቷ አዲስ አምባሳደር ሾመች።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምናሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡት አጋጣሚ ለጉዳይ ማረጋገጫ ቢጠየቅም ምላሽ ግን አልሰጡም።
ሆኖም ከሌሎች የሚኒስቴሩ የሥራ ኃላፊዎች ሀርጌሳ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት አምባሳደር ተሾመ ሹንዴ አምባሳደር ሆነው ስለመሾማቸው ዶቼ ቬለ ማረጋገጥ ችሏል። አምባሳደሩ ኬንያ ውስጥ በዲፕሎማትነት ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን ለሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ የሹመት ደብዳቤ ማቅረባቸውን ከሶማሊላንድ የወጡ ዘገባዎች አመልክተዋል። ተሾመ ሹንዴ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ባለፈው ሰኔ ወር ለ24 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሠራተኛ ለነበሩ ዲፕሎማቶች የባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር እና የአምባሳደርነት ሹመት ሲሰጡ አምባሳደር ሆነው መሾማቸውን ከአዲስ አበባ ሰሎሞን ሙጬ የላከው ዜና ያመለክታል።
ከሶማሊያ መንግሥት ጋር ውዝግብ ውስጥ የገባችው ኢትዮጵያ በሶማሊላንድ ለሚገኘው ቆንጽላ ጽሕፈት ቤት እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ልዩ መልዕክተኛ ብቻ ነበራት።
አዲስ አበባ፤ በኦሮሚያ ክልል ከሦስት ሺህ በላይ እስረኞች መለቀቃቸው
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የኢትዮጵያን የዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት በማድረግ ከ3,600 በላይ የሕግ ታራሚዎችን በይቅርታ መልቀቁን አስታወቀ። ይቅርታ ከተደረገላቸው ታራሚዎች መካከል 247ቱ ሴት ታራሚዎች ናቸው ተብሏል።
የኦሮሚያ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጉዮ ዋሪዮ እንደተናገሩት በይቅርታ የተፈቱት እስረኞች በወንጀል የተፈረደባቸውና በሕጉ አግባብ የባህሪ ለውጥ አምጥተዋል ተብሎ የታመነባቸው ናቸው።
«ባጠቃላይ ይቅርታ የተደረገላቸው የሕግ ታራሚዎች 3611 ናቸው። ለነዚህ ታራሚዎች ይቅርታ ለማድረግ በሕግ የተቀመጡ መሠረታዊ መመሪያዎችን ተከትለናል። ለአብነትም አንድ ታራሚ በሕጉ መሠረት የይቅርታው ተጠቃሚ ለመሆን በማረሚያ ቤት በቆየባቸው ጊዜያት ከፈጸመው የወንጀል ድርጊት ተጸጽቶ የታረመና ከተጎጂ ቤተሰብ ጋር መታረቁ ከታመነ ብሎም በታራሚው የሚቀረበው ጥያቄ በኮሚቴ ታይቶ ተቀባይነት ካገኘ ነው»
እንዲያም ሆኖ ከዚህ በፊት በፍርድ ቤት ነጻ ተብለው የነበሩና በእስር ላይ የሚገኙ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ከፍተኛ አመራሮች በይቅርታው ተካተው አለመቀቃቸውን የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ ገመቹ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።
«እነዚህ ተለቀዋል የሚባሉት በፍርድ እስር ላይ የነበሩ ናቸው። የእኛ ፖለቲከኞች ጉዳይ ግን ከዚህ ጋር አይያያዝም። ያለጥፋታቸው በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች ናቸው የሚል እምነትም ነው ያለን።»
በኦሮሚያ ክልል እየተስተዋለ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት በርካታ እስሮች እንደሚፈጸሙ ተደጋግሞ እንደሚነገር ከአዲስ አበባ ሥዩም ጌቱ በላከውን ዜና አመልክቷል።
ጄኔቭ፤ የተመድ 100
ሚሊየን ዶላር ድጋፍ !
የተመድ ሰብአዊ ቀውስ ጠንቶባቸዋል ላላቸው ሃገራት የ100 ሚሊየን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ማቅረቡን ዛሬ አስታወቀ። ከተመደበው ከዚህ ገንዘብ አንድ ሦስተኛ የሚሆነው የመን እና ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚከናወኑ የረድኤት ተግባራት ማንቀሳቀሻ የሚውል መሆኑ ተገልጿል።
ለየመን 20 ሚሊየን፤ ለኢትዮጵያ ደግሞ 15 ሚሊየን መመደቡን ያመለከተው ሮይተርስ የዜና አገልግሎት፤ በተጠቀሱት ሃገራት በርካቶች በረሀብ፤ በመፈናቀል፤ በበሽታና እና በተፈጥሮ አደጋዎች መጎዳታቸውን ጠቅሷል። በተጨማሪም ለማያንማር፤ ማሊ፤ ቡርኪና ፋሶ፤ ሄይቲ፤ ካሜሮን፤ ሞዛምቢክ እና ማላዊም ድጋፍ እንደሚደረግ አመልክቷል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ማስተባበሪያ OCHA ባለሥልጣን ጆይስ ምሱያ በቂ ድጋፍ አልተመደበላቸውም ላሏቸው የሰብአዊ ቀውሶች ከፍ ያለ እና ዘላቂነት ያለው ፈጣን ድጋፍ እንዲደረግ የለጋሾችን ትኩረት ይፈልጋል ብለዋል።
ጄኔቫ፤ የተመድ ወደ ባንግላዴሽ አጣሪ ቡድን ሊልክ መሆኑ
የተመድ ወደ ባንግላዴሽ አጣሪ ቡድን ሊልክ ነው።
የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን በቅርቡ ባንግላዴሽ ውስጥ በተማሪዎች የተመራውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ለማፈን በጸጥታ ኃይሎች የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን እንዲያጣራ መጋበዙን አስታውቋል።
በዛሬው ዕለት ኮሚሽነሩ ፎልከር ቱስክ፤ ጄኔቭ ላይ እንደተናገሩት የባንግላዴሽ ጊዜያዊ መሪ መሀመድ ዩኑስ በጠየቁት መሠረት አጣሪ ቡድን በሚቀጥሉት ሳምንታት ድርጅታቸው ይልካል።
የመንግሥታቱ ድርጅት በወቅቱ የተማሪዎቹ ተቃውሞ ወደ ጥቃት ተለውጦ 650 ገደማ ሰዎች መገደላቸውን ያመለክታል። በቅርቡ ያሰባሰበው መረጃም የሟቾች ቁጥር ሳይጨምር እንዳልቀረ ይጠቁማል።
ብራስልስ፤ የአውሮጳ ኅብረት ለዩክሬን ወታደሮችን ማሰልጠን መፈለጉ
የአውሮጳ ኅብረት ለዩክሬን ወታደሮች ለማሰልጠን እንደሚፈልግ አመለከተ።
ሆኖም ስልጠናው የት ይካሄድ በሚለው አባል ሃገራቱ እንዳልተስማሙ የኅብረቱ የውጪ ጉዳይ ኃላፊ ዛሬ አስታወቁ። ኅብረቱ በያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 60,000 የዩክሬን ወታደሮችን ነበር ለማሰልጠን ያቀደው፤ ሆኖም ውጊያው በመባባሱ ቁጥሩን ከፍ ለማድረግ መፈለጉ ነው የተገለጸው።
ኢትዮጵያዊዉ ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ
የቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴ ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው ትናንት ሐሙስ ነሐሴ 23 ቀን፣ 2016 ዓ.ም ማረፋቸውን ዩኒቨርስቲው አስታወቀ።
በኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ስፍራ እንደነበራቸዉ የሚነገረዉ ፕሮፌሰር እንድርያስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና በሌሎች ዓለማት ያስተማሩ አንቱታን ያተረፉ ምሁር ነበሩ።
ኢህአዴግ ሥልጣን ሲይዝ ከፍተኛ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁበት እና በተለያዩ ዩንቨርስቲዎች ፍልስፍና ሲያተምሩበት ከነበረበት ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ሀገራቸው በመመለስ ለጥቂት ዓመታት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ሆነው አገልግለዋል።
በወቅቱም የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ሲረቀቅ የአርቃቂ ኮሚሽን አባል የነበሩ ሲሆን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም አማካሪ ነበሩ።
ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴ የአንድ ልጅ አባት ሲሆኑ ሁለት ያሳደጓቸዉ ልጆች እንዳሏቸዉ የሕይወት ታሪካቸዉ ያስረዳል
ℹ️
DW Afrika
ℹ️
DW Afrika