ABREN MEDIA & Entertainment

ABREN MEDIA & Entertainment አብረን ሚዲያ፤ አብሮነት፤ ስነ ጽሁፍና ጥበብ፤ እድገትና ውበት፣ በነገር ሁሉ መልካምን እና ቀናን ነገሮች ፈልገን የምንገልጽበት መድረክ ነው።

https://youtu.be/y6cEBglaLL4?si=FULT_7Gg8nzlvOZV ከጋዜጠኛ ኤልያስ አወቀጋ ያደረኩት ክፍል አንድ ቃለ መጠይቅ።  አትሄጂም ስለተሰኘው መጽሃፌ ያደረግነው  ጠለቅ ያ...
12/15/2023

https://youtu.be/y6cEBglaLL4?si=FULT_7Gg8nzlvOZV ከጋዜጠኛ ኤልያስ አወቀጋ ያደረኩት ክፍል አንድ ቃለ መጠይቅ። አትሄጂም ስለተሰኘው መጽሃፌ ያደረግነው ጠለቅ ያለ ውይይት እንድታዳምጡ ጋበዝኳችሁ።

በደርግ ዘመን የነበረውን ክፉ ሕይወት... Nibab Television more :ቴሌግራም :- https://t.me/NahooT...

10/23/2023

እናውራ

ሰሞኑን አንዲት የምታምር ልጂ ምስል በፌስቡክ ላይ ሲመላለስና ባየሁት ቁጥር ልቤን ሲሰብረኝ ሰነበተ። ልጅቷ እራሷን እንዳጠፉችና የመጨረሻዋ ደብዳቤ ለፈጣራ እንደጻፈች የሚያሳይ አንጀት የሚበላ (dear God amen ) የሚል ምስል አብሮት አለ። በፈጣሪዬ እና በአሜን መካከል የሚታዩት የእንባዎችዋ ጠብታወች ያማሉ። ባገኘሗትና እቅፍ አርጌ አይዞሽ ይሄ ቀን ያልፉል ባልኳት! ከነችግርሽ የሚወድሽ አምላክ አለ ባልኳት! አለያም የጨነቀትን ነገር እንድትተነፍሰው ባደረኳት!! የሚሉ ስሜቶች ይፈጥራል!!!!

አሁን ለዚች ቆንጆ እረፍዷል። ምንም ማረግ አይቻልም። ምን ሆንሽ? ምን ልርዳሽ? ወደማንላት አለም ሄዳለች። ግን እሷ እየታገለች የነበረውን ትግል እየታገሉ፣ ሳይስቁ ስቀው ልባቸው እየደማ ትግል ላይ ያሉ ብዙ አሉ።

አንዳንዴ አይዞሽ/አይዞህ የሚባሉት አራት ፊደል ያላቸው ቃላት የሰውን ነፍስ ያተርፉሉ። አንዳንዴ ያች ደቂቃ እስክታልፍ አብሮ ለተቀመጠና ለታገሰ፣ ና ጆሮ ላበደረ ሰው ብዙውን ነገር ዘክዝከው አውርደው ተንፈስ ካሉ በሗላ፤ ለካ የኔ አለመኖር የሚቆጨው ሰው አለ ወደሚል ሐሳብ ይሻገራሉ። አንዳንዴ ደግሞ በየሶሻል ሚዲያው ቢለቀልቁት በየቀኑ ቢጽፉም ቢያነቡም የሚሰማ ጠፍቶ ወይኔ የሚያስብል ቦታ ያደርሰናል።

አምስተኛው መጽሐፌ "አብረን" ዋና ካራክተርዋ እሪስዋን ስለምታጠፉ። የእህቴን፣ የጋደኛዬን፣ ያክስቴን ልጂ ታሪክ ነው እንዴ የጻፍሽው የሚል አራት ወይም አምስት መልክት በየወሩ ይሰርሰኛል። እኔ የጻፍኳት የተፈጠረች ካራክተር ብትሆንም ብዙዎች ይሄ ህመም እንደሚሰማቸው ስለተረዳሁ የቀረጽኳት ገጸባህሪ ናት።

የእውነት ትግል ውስጥ ያሉትን እንዴት እንርዳቸው። ከቀን ወደቀን ቁጥራቸው እየጨመረ ነው። አላየሁም አሉ የምንልበትን ሰአት አልፈናል። እና እናውራ!

ምልክቱ ምንድነው? ከጠረጠርንስ ምን እናርግ? ሌሎችም ሌሎችም ሃሳቦችን አክሉበት እና እንወያይበት።

#እመቤትመንግስቴ #ዝምከምልብዬ #አብረን #በቃ

09/26/2023

ዳንደላይን

በጨዋታ መሐል እትዬ ጥሩወርቅ "ይሄ ደፉር ዛሬ ጠዋት ያለኝን ጉድ ልንገራችሁ" ብለው ጀመሩ።

"ምነ አለሽ"ብለው ቡና ሊጠጡ የተሰበሰቡት ሴቶች ጠየቁ።
እትዬ ጥሩ (የሰፈሩ ሰው እንደሚጠራቸው) ቤታቸውን ተከራይቶ ስለተቀመጠው የኪውባ ወታደር ሲያወሩ ሁልግዜም "የኔው ቤት ጉደኛ "ይጨምሩበታል። ስለሱ ሲያወሩ የሰፈር ሰው በመገረም ሲለሚያዳምጣቸው ሳይጨማምሩበት አይቀሩም።

እትዬ ጥሩ ባላቸው ከሞቱና ንብረታቸውን ከተወርሱ በሗላ መንግስት ከሚሰጣቸው ሁለት መቶ ሐምሳ ብር ውጭ ምንም ገቢ ያልነበራቸው፤ የተወሰነውን የሰርቪስ ክፍል አከራይተው ለተከራዩት ሰወች ምግብ እየሰሩ ነበር የሚተዳደሩት።
ከነዚህ ሰወች መሐል ሄሱዝ የተሰኘ የኪውባ ወታደር አለበት። የኔው ጉደኛ የሚል ቅጽል ስም ቢሰጡትም ለትዬ ጥሩ ሁሉ ነገሩ ያስገርማቸዋል። እማማ ጥሩ ስለ አበላሉ፣ ስለ አለባበሱ፣ ስለደግነቱ፣ ስለ ቋንቋውእና ስለ ሁሉም ነገር ማውራት ይወዳሊ።

"ምን ቢልሽ ነው ዛሬ በጠዋቱ እንዲህ የተንተከተክሽው" አሉ እትዬ የሺ።

"ሆ " ብለው ጀመሩ እማማ ጥሩ።
ቁርስ አቀረብንለት፣ የጨዋ ቁርስ ለዛውም። ሳይበላው ተነሳ። ምነ ሆነሃል ብለን ጠየቅነው። ሰለቸኝ አላለንም!! ሁሌ የምታቀርቡት አንድ አይነት ነው። አንዳንድ ቀን ሌላ ነገር ለምነ አትሰረሩም አለን! ጉድ እኮ አያልቅም ብለው ሳይጨሬሱ።
የሰፈሩ ሴቴቹ በሙሉ አንድ ላይ ተንጫጩ። "ተናቅን፤ ምግባችን ተናቀ በሚል አነጋገር ተያዬ።" እድል ቢያገኙ እና አቅም ቢኖራቸው የሚደበድቡት ይመስል ነበር።

"መች እሱ ብቻ" አሉ እትዬ ጥሩ። አገራችን ድሐ ናት አንተ የለመድከው ምግብ የለንም ስንለው ምን ቢመልስ ጥሩ ነው። "ድሐ አይደላችሁም ጥጋበኛና፣ በጣም መራጮች ናችሁ፣ ከዚያ በላይ ደግሞ ብዙም ለአዲስ ነገር ቦታ አትሰጡም አለን።" የይንቨርስቲ ተማሪ ልጃቸው ያስተረጎመችውን እየደገሙ። እውጭ ወጥቶ ከዛፍ ላይ ኮክ አራግፎ እሱን እየገመጠ ሄደ አሉ እማማ ጥሩ።

የስድብ ናዳ ከሰፈሩ ሴት ወረደበት። "ይበለው ከኛ ቅንጬ እና ፍትፍት ደረቅ ኮክ ከመረጠ ምን አገባን።" ያድርቀውና፣ "የአህያ ስጋ ከአልጋ ሲሉት ከአመድ" አሉ ተባባሉበት።

ምን እሱ ብቻ። ይሄ ቅጠል ልጆቹ የሚጫወቱበት ጢቢ ጢቢ የሚሉት አይቀረው፣ የውሻ ምላስ ብለን እንደ አረም ነቅለን የምንጥለው አይቀረው። ቀቅላችሁ ካላመጣችሁ እያለ መከራችንን ነው የሚያሳየን። እመ ብርሐን ሰተት አርጋ ወደመጣበት ተመልሰው እንጂ አሉ። ሌሎቹን ጎረቤቶች አይን አይን እያዬ።

እውነቱን ለመናገር እንዲሄድቤቸው አይፈልጉም። የሌሎቹ ሶስት ተከራዮች ሂሳብ በአንድነት ተደምሮ እሱ የሚከፍላቸውን አይተካከልም። በእጥፍ ነው የሚከፍላቸው። ደግ ነው ምናምን ከውጭ ገዝቶ ከገባ ሳያካፍላቸው ወይ ለሱ የገዛውን ለሳቸው ሲይገዛላቸው አይቀርም። ከዚያም በላይ በጎረቤቶች ዘንድ ተደማጭነትን ሰጥቷቸዋል። ባፋቸው የሚናገሩትን ልባቸው ባያምነውም ከመናገር ወደሗላ አይሉም።

ሰሞኑን የሰፈሩን ቡና ጨዋታ ማሰላሰል ጀምሬአለሁ። በተለይ ደግሞ የሱ (ኢሱዝ ለማለት የሚጠቀሙበት ስም) አደረገ የሚባለውን።

አንድ ጤናን በተፈጥሮ መንገድ የሚል ኮንፍረንስ ተካፍዬ ስለ ዳንደላይን (የውሻ ምላስ) ጥቅም በጣም በከባድ ሰማሁ። ስለ ሳማም እንደዛው። ጢቢ ጢቢ ቅጠል፣ ስለ ሚጥሚጣም ሌሎችም ሌሎች ቅመማ ቅመሞች ጠንከር ያለ ሙገሳ ስሰማ ዋልኩና ከዛሬ አርባ አመት በፊት የሰማሁትን ወሬ አስታወሰኝ።

እኔ የምኖርበት አካባቢው ካለ የጤና ምግብ አቅራቢ (whole food) የውሻ ምላስ በውድ ዋጋ ገዛሁ። እንዴት አርጌ እንደምሰራው ብዙ ባላውቅም ይሄን ያህል ጥቅም ካለው በሚል ነበር። እንደ ጎመን ሸርድጄ ቀቀልኩት። ጣእሙ ያው ጎመን ሆኖ አገኘሁት። ከዛሬ ጀምሬ ምግቤ ውስጥ እንደማጠቃልለው ለራሴ ነገርኩ።

ሁለት ነገር ተማርኩ። እናቶቻችን የትኛውም የሳይንስ ወረቀት ከመታተሙ በፊት ጠንቅቀው ያወቁት ቅመማ ቅመም ትልቅ ሐብት መሆኑን እና አዲስ ነገር ደፍሮ መሞከርን አስፈላጊ መሆኑን።

#እመቤትመንግስቴ #ዝምከምልብዬ #አብረን #በቃ

09/21/2023

ዝም አልልም

ነግረውኝ ነበር ደግመው ደግመው
ዝም በይ ዝምታ ወርቅ ነው

አይኔ እያየ ክፉን ነገር
ዝምታ ወርቅ ነው ብዬ ባልናገር

ማን ይሆን ወንጀለኛው?
ማን ይሆን ባለ በደል?

እኔ እያየሁ ያላየሁት ሰምቼ ያልሰማሁት
ወይስ እነሱ ዝም በይ ዝምታ ወርቅ ነው ያሉት

#ዝምከምልብዬ #በቃ #እመቤትመንግስቴ #አብረን

05/01/2023
ጎራ በሉ
11/14/2022

ጎራ በሉ

10/18/2022

ያቀ ዛሬ ሆነ

አንድ ወቅት ላይ የምኖርበት አካባቢ ያለ የደራሲያን ስብስብ የሚሰጠው የአምስት ቀን ስልጠና ላይ እንድገኝ ተጋበዝኩ። እውነት ለመናገር በዚህ ደረጃ ያለ ስልጠና ስካፈል የመጀመሪያ ጊዜዬ ሰስ ነበር፤ ምን እንደሚጠብቀኝ በፍጹም አላወኩም። ግን በመጋበዜ ከልክ ያለፈ ተደስቼ የሚመጣውን ሁሉ ለመቀበል እራሴን አሰናዳሁ።

የመጀመሪያው ቀን ገብተን እንደተቀመጥን የእለቱ መምህር በፈገግታ ተቀበለን። አጠር ያለ ንግግር ከአደረገ በሗላ፣ አምስት አምስት እሩብ ካርዶች (3×5) ለሁላችንም አደለን እና ህይወታችሁን በአምስት ምእራፍ ከፋፍላችሁ፤ ታራካችሁን በነዚህ አምስት ካርዶች ላይ አስፍሩ የሚል ቀጭን ትዛዝ አከለበት። እዚያ ላይ ቢያቆም መልካም ነበር ግን ከአምስት ቀን በሗላ የፕሮግራሙ የመጨረሻ ቀን ስመለስ ሁላችሁም የጻፋችሁትን መድረክ ላይ ለማንበብ ተዘጋጁ ብሎ ፈገግ አለ።

ብዙዎቻችን ግራ በመጋባት ተያየን። ምን ማለቱ ይሆን? በነዚህ የወረቀት እሩብ አምስት ካርዶች ላይ ሰው የህይወት ታሪኩን እንዴት አርጎ ማሳረፍ ይችላል? እርስ በርሳችን ተፉጠጥን።
እውነት ለመናገር ከየት ጀምሬ፣ የቱን አንስቼ፣ የቱን እንደምተወው ማሰብ ጀመርኩ። ለኔ አይደለም የህይወት ታሪክና ያለፈውን ሳምንት ለመግለጽ በቂ ቦታ የተሰጠኝ ስላልመሰለኝ መጨነቅ ጀመርኩ።

መምህሩ መደናገራች የገባው ይመስል፤ አንድ እናንተ የተቀመጣችሁበት ቦታ ላይ የነበረች ሴት የጻፈችውን ታሪክ እንደ ምሳሌ አነብላችሗለሁ አለና ለኛ የሰጠንን የሚመስሉ አምስት እሩብ ካርዶችን አውጥቶ ማንበብ ጀመረ።

የወረቀቱ ባለቤት "ፖርሻ ኔልሰን" ትባላለች። አንድ አንድ ወቅት ላይ ልክ ዛሬ እንደተሰበሰብነው ሰዎች ይሄው ጥያቄ የቀረባላት ጸሐፊ ስትሆን፤ መልስ ስትሰጥ የህይወትዋን በአምስት ምእራሮች እንደሚከተለውም ውብ አርጋ ስላስቀመጠቻቸው ለሌሎች ተማሪወች በምሳሌነት እንደሚጠቀሙባቸው ከነገረን በሗላ መምህራችን አነበበልን።

ምእራፍ አንድ

በአንድ ጎዳናላይ ስጓዝ የተቆፈረ ጉድጓድ ነበር። አላየሁትም! ወደኩ። ከዚያ ጉድጓድ ለመውጣት ብዙ ግዜ ፈጀብኝ። ብዙም ተሰቃየሁ። ግን የኔ ስህተት አይደለም። ጉድጓዱን የቆፈሩት ሰወች ስህተት ነው በሚል እራሴን አጽናናሁ። የልጅነት ጊዜዬን አብዝቶ አስታወሰኝ።

ምእራፍ ሁለት

በዚያው ጎዳና ላይ እራሴን አገኘሁት። የተቆፈረው ጉድጓድ አሁንም አለ። አላየሁም አሉ ብዬ መንገዴን ቀጠልኩ። እንደገና እዛው ጉድጓድ ውስጥ ወደኩ። የገዛ ጥፋቴ ነው ብዬ ተነጫነጭኩ። አሁንም እረጂም ግዜ ወሰደብኝ። ልጅነቴን ሳይሆን አሃያወቹን እድሜዬን አስታወሰኝ።

ምእራፍ ሶስት

እራሴን እንደገና እዛው መንገድ ላዬ አገኘሁት። የተቆፈረው ጉድጓድ አሁንም አለ። በደንብ አርጌ አይቼዋለሁ። ግን ልማድ አይደል እንደገና ወደኩ። መውጣቱን ስለተለማመድኩት ብዙ ግዜ አልፈጀብኝም። ጥፋቱ የኔ እንደሆነ እና መጠንቀቅ እንዳለብኝ ለራሴ መከርኩት። ወደ ስላሰዎቹ ቁጥሬ የዞረ መሰለኝ።

ምእራፍ አራት

እዛው መንገድ ላይ እራሴን አገኘሁት። የተቆፈረው ጉድጓድ አሁንም አለ። ተመልሼ እዛው ጉድጓድ ውስጥ እነዳልወድቅ እጂግ በጣም ተጠንቅቆ አለፍኩ። እራሴንም ሆነ ሌሎችን መውቀስ አቆምኩ። ህይወት ላይ ያለኝ አመለካከትም ሆነ እድሜዬ ከፍ ብሎ አገኘሁት።

ምእራፍ አምስት

መንገድ ጀመርኩ። ቆም ብዬ ሳስብ በሌላ መንገድ መሄድ እንደምችል ስለተረዳሁ ያንን የተቆፈረ ጉድጓድ ያለበትን ትቼ በሌላ መንገድ ጉዞዬን ጀመርኩ። አሁን ሲገባኝ ይሄ እጂግ በጣም የተሻለ መንገድ ነው። ህይወት ትልቅ ትምህርት ቤት ነው። ከመንገዶችም ሁሉ የተሻለው ነው። የተቆፈረ ጉድጓድ የሌለበትን መንገድ መፈለግ የኔ ስራ ሆኖ አገኘሁ።

በመገረም እና በጥሞና አዳመጥኩት። መጽሃፍ ብትጽፍ እና ብዙ ሐተታት ብታስቀምጥ ከዚህ የላቀ ልታስተምረኝ እንደማትችል ተረዳሁ። ያላሰብኩት እንባ በፊቴ ላይ ሲወርድ ሙቀቱ ተሰማኝ።

ተራዬን ለመጻፍ ጀመርኩ

ምእራፍ አንድ

የተወለድኩት ኢትዮጵያ የምትባል ውብ ምድላይ ቢሆንም፤ ለግዜው ደርግ የሚባል የተሸቀበ እድል ገጥሟታል። የትኛው ደግ፣ የትኛው ክፉ ሰው መሆኑንን ለይተን ማወቅ ያቃተን ወቅት ላይ ያለነው። ቤተሰቦቻችን በየቀኑ ለቅሶቤቴ፣ በየቀኑ ጥቁር ልብስ፤ በየቀኑ ቀብር የሚውሉበት ምድር መሆኑን ተረዳሁ። የኔና የብጤዎቼ እድል እንደ ህጻን በመቦረቅ ፈንታ፤ ከረሜላ እንደተቀማ ልጂ በማናውቀው እና ባልገባን ችግር ቀን በቀን በሐዘን የተወረረ ሆነ። ከኔ የተሰረቀውን ወይም የተቀማነውን የልጅነት ዘመኔ ብዬ አሰብኩት።

ምእራፍ ሁለት

ችግሩ እየባሰ ነው። ብዙ ወላጆች ልጆቻቸውን አብዮት ለተሰኘ ሰደድ እሳት ገበሩ። የኛ ወላጆች ደግሞ ነገ እጣው የኛ እንዳይሆን ሰግተው የቀን ተቀን ህይወታቸው በፍርሐትና በማሸማቀቅ የተሞላ ሆነ። ለመኖር እና የመኖርን ነጻነት ለማወቅ ይህቺን ኢትዮጵያ የምትባል ምድር በቦሌም በባሌም መላቀቅ እንዳለብን ተረዳን። ዛሬን ያላየ ለነገ አይኖርም የሚለው እውነት በየመንገድ ላይ ወድቀው በምናያቸው ታላላቆቻችን አስከሬን ይገለጽ ጀመር። ስደት እውነት ሆነ። ከእናት አባቴ፤ ከእህት ወንድሞቼ፤ ከማውቀው ሁሉ ነገር ተለይቼ ወደ ማላውቀው አለም አመራሁ። ልጅነት አበቃ!!

ምእራፍ ሶስት

ስደትንና ከስደት ጋር አብረው የሚመጡትን መልካምና መጥፍ ገጾች መለማመድ ጀመርኩ። ናፍቆትን፣ ከሚወዱት ቤተሰብ መለየትን እና አዲስ ባህልን፣ አዲስ ቋንቋን እኩል መለማመድ ጀመርኩ። ቢሆንም እኔ የትኛው ቦታ ላይ እንዳለሁ፣ ወይም ለየትኛው አለም እንደተጻፍኩ በፍጹም ማወቅ አልቻልኩም። ማንነቴን ፈልጌ ለማግኘት እየታገልኩ ነው።

ምእራፍ አራት

አዲሱ አለም የሰጠኝን ጸጋ መቀበል ብችልም አገሬን ግን መርሳት አልቻልኩ። ግን የተሰጠኝን እድል መጠቀም እንዳለብኝ ተረዳሁ። ሁሉንም መልካም ነገር ባየሁ ቁጥር እንዴት አርጌ ወደ አገሬ እና እኔ ወደ ምወደው ምድር ለመውሰድ እንደምችል ማሰብ ጀመርኩ። ግንድ ውሐ ላይ ቢንሳፈፍም አዞ ግን መሆን አይችልም የሚለው የአገሬ ብሂል፤ አገሬ ብዬ የተቀመጥኩበት አገር የሰው አገር መሆኑን ሌት ተቀን እያስታወሰ ያስጨንቀኝ ጀመር።

ምእራፍ አምስት

የነጻው አለም ብዙም ነጻ ያልሆነ፣ ሰወችን በብቸኝነት እና በፍቅር እጦት፤ በእኔ እበልጥ እኔበልጥ ፉክክር አስሮ፤ አንድ እርምጃ ወደፊት ሳያራምድ ባሉበት የሚያስረግጥ፣ እደርሳለሁ በሚል ተስፋ የሚያመላልስ፣ የሚያዩት በርግጥ ግን የማይጨብጡት፣ የህልም ህልም መሆኑን ተረዳሁ። ይህን ማወቄም ለአገሬ እና ለተወለድኩባት ምድር የተለየ ፍቅር ሰጠኝ። እኔን ፈልጌ አገኘሗት። ነፍሴ ምድር ላይ ለተፈጠሩ የሰው ልጆች በሙሉ በፍቅር ሰገደች፤ ከፍቅር የላቀ ምንም ሐይል የማትሻ ሆና አገኘሗት።

አምስቱን ምእራፎቼን ሲደመድም ከዚህ የተሻለ ነገር ይኖረኝ ይሆን? ግን ለግዜው የለኝም። አንብቢ ቢለኝ ይሄን ላንበው ነው? አላነበውም!! ሌላ የተሻለ ነገር መጻፍ እችል ነበር? ወይስ ያለኝ ይሄ ነው? አምስት ምእራፍ በጣም ትንሽ ነው ለዛውም እያንዳንድ ምእራፍ ከሩብ ገጽ ያልበለጠ። ከራሴ ጋር ትግል ጀመርኩ።

መምህሩ የመጀመሪያ ቀን የሰጠንን የቤት ስራ ሊሰበስብ ተመለሰ። የልቤ ምት መጠኑ በጣም እንደጨመረ ተረዳሁ። አሁን አንብቢ ቢለኝ ምን ልል ነዉ።

መጨነቄ የገባው ይመስል ትኩር ብሎ እያየኝ። ዛሬ መድረክ ላይ ወጣችሁ አንብቡ አልላችሁም። ግን ስትወጡ በሩ ላይ ሶስት ምርጫ አላችሁ አንዱን ተጠቀሙ አለ።

የመጀመሪያው የያዛችሁትን ወረቀት በስተቀኝ በኩል ያለው እሳት ውስጥ ማቃጠል ነው። ይሄንን ለሰውም አላሳይም አልናገረውም እዚሁ ትቼው ነው የምሄድ የሚመጥነኝ ካላችሁ፤ ይሄን ተጠቀሙ።

ሁለተኛው ደግሞ በስተግራው ያለው ሳጥን ውስጥ በፖስታ ከታችሁ ማስቀመጥ ነው። አንብቤ አስተያየት እሰጣችሗለሁ። እይታችሁን አብረን እንቃኛለን።
ሶስተኛው ደግሞ ሳታቃጥሉ ወይም ለኔ ሳትሰጡ የጻፋችሁትን ይዛችሁት መሄድ ነው። ምናልባት አንድ ቀን መጽሐፍ ታርጉት ይሆናል። እሱም ካልሆነ ለሌላ ሰው የራሱን አምስት ምእራፍ እንዲጽፍ እድል ትሰጡበት ይሆናል አለን።

በፍጥነት ይመታ የነበረው የልቤ ጋብ አለ። ለመወሰን የነበረኝ ግዜ እረጂም ባይሆንም የተሰጠኝ ምርጫው አስደሰተኝ። ምእራፎቼን ሰብስቤ በቦርሳዬ ከትቼ ወደቤቴ አመራሁ። አንድ ቀን እናንተም ለሌላው አምስት ካርድ ትሰጡ ይሆናል ያለው የመምህሩ አነጋገር አብሮኝ ቆየ።

የጻፍኩትን ደጋግሜ አየሁት። ከዚህ ቀደም በውስጤ ተቀብረው የነበሩ ብዙ ነገሮች ወደላይ ያኮበኩቡ ጀመር። ሌላም ሃሳብ ደጋግሞ ወደ አእምሮዬ መምጣት ጀመረ። ታሪካችን ሳንፈራ ሳንደብቅ በራሳችን አንደበትና ብእር ብንጽፈው፤ ብንናገረው ምን ይመስል ይሆን?

የተሰጠኝ የቤትስራ ዋናው አላማው አሁን ገና ቁልጭ ብሎ ታየኝ። አንድቀን አምስት ካርድ ለሌላ ትሰጡ ይሆናል ያለው የመምህ ድምጽ አስተጋባ። ያንን ንድ ቀን ዛሬ ሆኖ አገኘሁት። እነሆ አምስት አምስት ካርድ አደልኳችሁ። እራሳችሁን በርብሩ።

#እመቤትመንግስቴ #አብረን #ዝምከምልብዬ

My beautiful Sara, you are God's gift to me. I am blessed to be given a chance to call you my child, my sister, my frien...
10/09/2022

My beautiful Sara, you are God's gift to me. I am blessed to be given a chance to call you my child, my sister, my friend and my mirror. I love the strong woman you become. Your, love care and kindness for other human beings amazes me everyday. You are a joy to be around and I love you. Happy Birthday. Enjoy your day.

10/07/2022

ጭስ መውጫ

ከማልረሳቸው የልጅነት ትውስታዎች አንዱ፣ ከሞት ያመለጥኩበት ሌሊት ነው። አንድ ከባድ ዝናብ ጥሎ አጥንት የሚሰብር ብርድ የተከተለበት ምሽት እናቴ እስቲ እባካችሁ ከሰል አቀጣጥሉ እና አምጡ ትንሽ ይሙቀን አለች።
ከሰሉ ዝም ብሎ ከሚቃጠል ተብሎ ቡና ተፈላ። ሰብሰብ ብለን አንድ ክፍል ውስጥ ስንስቅ፤ የሰው አንድ ክፍል መሰብሰብ የከሰሉ ሙቀት፤ ሳቅና ጨዋታው ተጨምሮ ብርዱን እረስተነው አመሸን።
ቡናው አልቆ ሁሉም ወደ ክፍሉ ሲያመራ ግን አጂሬ ብርድ ተመልሶ ከተፍ አለ። እኔ ብልጥዋ አንድ መአት ከሰል ማንደጃው ላይ ጨምሬ ጎትቼ መኝታቤቴ አስገባሁት። ማንደጃውን ከጎኔ አስቀምጬ ትንሽ እሳት ከሞኩ በሗላ እንቅልፍ ድብን አርጎ ወሰደኝ።

ስነቃ ቤተሰብ ከቦኝ፣ ግማሹ ሲያለቅስ ግማሹ ደግሞ ውሃ ሲረጨኝ፣ ሌላው ወተት አግቷት ጢሱ ከውስጧ ካልወጣ ሰው አትሆንም ሲል፤ እኔ ደግሞ እውነት የተከሰተ ነገር ይሁን በህልም የተከሰተ መለየት አቅቶኝ ተፋጠጥን።
ቁም ነገሩ ያን ለት ሞትን አመለጥኩት። ወይም ደግሞ የተጠራሁበት ቀን አልነበረም ተመልሼ ከነዋሪዎች ተቀላቀልኩ። ያን ቀን ትልቅ ትምህርት ተማርኩ። የጭስ መውጫን ጥቅም እና መውጫ ያጣ ጥስ ሊገል እንደሚችል።
ሰሞኑን የተማርኩት ታላቅ ነገርም ከዚህ ቀን ትምህርቴ በምንም አይለኝም። በህይወታችን ውስጥ ያሉ አላስፈላጊ ነገሮች ሁሉ እንደ ጢሱ መውጫ እንደሚያስፈልጋቸው ተረዳሁ።
ተፈጥሮ ለብዙው አላስፈላጊ ነገር መውጫ የሰጠችን ቢሆንም እኛ መርጠኝ መውጫ የከለከልናቸው፤ (እኔው በገዛጄ መውጫ አሳጥቼ ሊገለኝ አስቦ እንደነበረው ጢስ) በየቀኑ የሚገሉን ብዙ ነገሮች ተሸክመናል።

ምግብ አስፈላጊነቱን ሲጨርስ ከሰውነታችን እንዲላቀቅ ተፈጥሮ መውጫ አዘጋጂቶለታል። ውሐም በዚሁ መልክ የተለገሰው መውጫ አለው። ብዙዎች ነዳጂ የሚያቃጥሉ ነገሮች በሙሉ ጥስ መውጫ አላቸው። ለምሳሌ መኪና፣ አይሮፕላን፣ ባቡር እያልን ልንደረድራቸው እንችላለን።
የሚያሳዝነው ግን ለብዙ ህመሞች ቀስቃሽ ለሆነው ነገር መውጫ አለመስጠታችን ነው። ብዙዎቻችን መርጠንም ይሁን ወይም እንደኔ ከሰል ሳናስበው አዘናግቶ ወደ ውስጣችን ለገባው ጥላቻ መውጫ አጥተንለታል።

በቅርብ ያነበብኩት አንድ የሳይንስ ምርምር፤ አንድ ሰው ከውስጡ ሰላም ባጣ ቁጥር ወይም እራሱን ወደ ጥላቻ፣ በቀል እና ቅያሜ በመራ ቁጥር የደሙን ባላነሰ ይቀይረዋል ይላል። ቀስ በቀስ በጥላቻ መመረዝ ሌላውን ከሚጎዳው የላቀ እኛኑ ያዳክመናል።
ታዲያ እንዲህ ላለው ከባድ ነገር መውጫ እንዴት አጣንለት? ለጥላቻስ እራሳችንን እንዴት አሳልፈን ሰጠን? በቀልና ቅያሜስ በውስጣችን ያለ ከልካይና ያለ መውጫ እንዲዘዋወሩ እና መልሰው እኛኑ እንዲያጠቁን ለምን ፈቀድንላቸው?
ጭስ መውጫ፣ ነገር መውጫ ወይም የሰላም በር ልንለው የምንችለው እራሳችንን ከአላስፈላጊ እና አስጨናቂ ከዚያም አደገኛ ነገር የምናላቅቅበት የፍቅር በር ለሁላችንም አስፈላጊ ነው። እንዴት እና ወዴት እንደምናገኘው ለያንዳንዳችን የተለያየ መንገድ ቢኖረውም! መውጫ መሻቱ ግን ለሁላችንም መጀመሪያ ስራችን ብናደርገው መልካም ነው እላለሁ።

እመቤት መንግስቴ
#ዝምከምልብዬ #አብረን

09/20/2022

።።። ከአንባቢያን የተሰጡ አስተያየቶች።።።

አብረን
ደራሲ እመቤት መንግስቴ

የልብ-ወለድ መጻሕፍት ማንበብ ካቆምሁ ብዙ ጊዜ ሆኖኝ ነበር:: ከብዙ ዓመታት ወዲህ የሚስበኝ ግለ ታሪኮችና የዕውነተኛ ኹነቶች ዘገባ ቢሆንም፣ ይኽ የእመቤት መንግስቴ አብረን የተሰኘ ልብ-ወለድ መጽሐፍ ግን ስሜቴን ሊስብና አእምሮዬን ሊሰቅዝ ቻለ:: የ 8 ምናባዊ ሴት ጓደኛሞች ታሪክ ነው:: የተዋወቁት ኢትዮጵያ ውስጥ ገና ተማሪ ልጆች ሆነው ነው:: የገጸ ባህርያቱ ተክለ ሰውነት አሳሳል የተዋጣለት ነው::
የእመቤት የባህርያት አቀራረጽ ሥልት፣ በባለ ታሪኮቹ ላይ እውነተኛ የሚመስል ሕይወትና ነፍስ ይዘራባቸዋል:: አንባቢ በምናብ ያያቸዋል::

ደራሲ እመቤት በገጸ-ባህርያቱ አማካይነት በዕውን ዓለም የሚኖሩ ጓደኛሞች ከልብ እንዲረዳዱና ለችግሮቻቸው መፍትሔ እንዲፈልጉ መልዕክት ታስተላልፋለች:: የተዋጣላትም ይመስለኛል:: የሥነ-ጽሑፍ ጥበብ የሕይወት ለዋጭነቱና የሚመሰገን የአጻጻፍ ዘይቤም በመጽሐፉ አተራረክ ውስጥ ይታያል::

ዶ/ር ፈቃዱ ፉላስ (ፒ.ኤች.ዲ.)
ሲልቨር ስፕሪንግ፣ ሜሪላንድ፣ ዪ.ኤስ.ኤ.

።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።

አብረን
ደራሲ እመቤት መንግስቴ

ይህ መፅሀፍ በግልፅነት ላይ ተመስርተን በችግሮቻችን ላይ በጋራ ብንዘምት በተለይ በብቸኝነት እሚጨምቀን ን ችግር ለማቃለል ያግዘናል ።

ደግ ሰዎች ሞተውም እንደሚያኖሩን ሁሉ ይገለፅልናል ።

እሙዬ ድንቅ በረከት ነው ። ለደጓ ሰዊ እኔም ዋንጫዬን አንስቻለሁ ።

በራሱ ላይ መንቃት እሚሻ ይዝመትበት !

ደራሲ ስንዱ አበበ

።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።

የእመቤት መንግሥቴ የአብረን መጽሐፍ

አነቃቂ – ሥራ ፈጣሪ – የዓለም ዓቀፋዊ ሰላምና አብሮነት አቀንቃኝ – ሴቶች መሪ እንዲሆኑ ሞጋች ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

ኑሮዋችንን እንዲያቀላጥፍ የተዳበልነው ቴክኖሎጂ ልብ ካላልነው ልንገታ የማንችለው አጉል ሱስና እኛኑ መልሶ የሚዋጋ የጦር መሥሪያ መሆን ይችላል:: የእመቤት መንግሥቴ የእብረን መጽሐፍ የሕይወታችንን ቃናና ስብዓዊ አብሮነታችንን ነቅተን እንድናጠናክር አንቂ ደውላችን ነው::

ይህችን ሙገሳ ከመጻፌ በፊት የእመቤት መንግሥቴን የአብረን መጽሐፍ አምብቤ የመጽሐፉን መልዕክት ተግባራዊ ማድረግ ፈለግሁ:: አወንታዊ ለውጥ በዘላቂ የእስተሳሰብና የባሕሪ ለውጥ (habit formation) ይረጋገጣል::አልፎ አልፎ የምናደርገው የሞቅታ የአስተሳስብና የባሕሪ ለውጥ ጠቃሚነቱ ወደ ዘላቂነት ሲሸጋገር ብቻ ነው::

ታዲያ መጵሐፉ የሚጠቁማቸውን የአስተሳሰብና የባሕሪይ ለውጦችን ማጤን ጀመርኩ:: መለወጥ የምችለው እኔን ስለሆነ የኔን አስተሳሰብና ባሕሪ ማሰላሰልና መገምግም ላይ እገኛለሁ::

እኔን እንደገባኝ የአብሮነት መልዕክት በሚከተሉት ተግባራት ይገለጻል:: የሚቀርቡንን ሰዎች በውስጣዊ ጆርዋችን ማዳመጥ:: በውይይታችን ወቅት ግንዛቤያችንን የሚጨምሩ ጥያቄዎችን መጠየቅ:: ለጥያቄ መልስ ከመስጠታችን በፊት ጥያቄውን መረዳት:: ከእለታዊ የሩጫ ሕይወት መካከል ሰከን ያለ ጊዜን መፍጠር:: ስንገናኝ ውይይታችን ከወቅታዊ ጉዳዩች ይልቅ ለበለጠ የእርስ በርስ ትውውቅ ጊዜ መስጠት:: ከሚቀርቡን ሰዎች ጋር ስንጨዋወት በሚያስማሙን ነገሮች ላይ ማተኮርና የመሳሰሉት ናቸው:::

መጽሐፉ ተለቅ ተለቅ ያሉና የሚያስማሙን ምልከታዎችንና ትርጉሞችን ይጠቁማል:: ከነዚህ ተለቅ ያሉ መልዕክቶች አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው:: አብረን ይሻለናል:: አንዳችን ለሌላችን መድሃኒት ነን:: አንዳችን ስንወድቅ ሌላው ያነሳናል:: መደማመጥ ግንዛቤን ያመጣል:: አብሮነት እንድ መሆን ማለት አይደለም:: አብሮነት አንዳችን የሌላውን ብሶት ሳንፈርድ ማዳመጥና ነገሮችን በተናጋሪው ዓይን ማየት ነው::

የመጽሐፉን የአብሮነት ሚስጥረ መልዕክቶች እያንዳንዱ አንባቢ በተረዳውና በመረጠው መንገድ ተግባራዊ ማድርግ ይገባዋል በሚል እምንት እኔም የሚከተሉትን ባሕሪያት አጉልቼ እንድለማመድ አነሳስቶኛል:::

ለማጠቃለል የእመቤት መንግሥቴ የእብረን መጽሐፍ በመተጋገዝ በመደማመጥ በመቀራረብና በመተሳሰብ ሕይወትን በአብሮነት እንዳጣጥም አነቃቅቶኛል::

ዶ/ር ጌብ ሐምዳ (ፒ ኤቺ ዲ)
ደራሲ

።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።

አብረን
ደራሲ እመቤት መንግስቴ

በተለየ መንገድ ማድረግ የምንችላቸው ብዙ ነገሮች አሉ ፤ ነገር ግን ወደ ኋላ ተመልሰን የማንለውጣቸው ግን ደግሞ ተምረንባቸው እኛነታችንን የሚሰሩ ነገ'ችንን ቆም ብለን እንድናስብ የሚያደርጉ ይሆናሉ፡፡

ደራሲና ገጣሚ እመቤት መንግስቴ አብረን በተሰኘወው አዲስ መጽሐፏ ይህን ሃሳብ ለነፍሳችን በቀረቡ ስምንቱ ሴቶች ውስጥ እንድናየው ፈልጋለች፡፡ ‘አትሄጂም’ እና ‘ዝም ከምል ብዬ’ በሚሉት መጽሐፎቿ ውስጥ ሴትነትን በተለየ መነጽር እንድናየው አግዛን ነበር፡፡

በአብረን መጽሀፏ ውስጥ ግን በሽንፈት ውስጥ ጥንካሬ ፤ ባለማስተዋል ውስጥ ጥበብን፤ በጠፋ ማንነት ውስጥ ሰው የመሆን ሚስጥርን ከሴትነት ጀርባ እንድንፈልግ ጋብዛናለች፡፡ ስምንቱ ሴቶች በጓደኝነት ብቻ የሚታሰር ማንነት እንደሌለ በእያንዳንዱ ምዕራፍ ውስጥ ይነግሩናል፡፡ ጓደኝነት ይገዝፍና የምንናፍቀውን ሰውነትን…ሰው የመሆን ሚስጥርን ይገልጽልናል፡፡

በዚህ እህል በተውደደበት ሰው በረከሰበት ዓለም ሰው ሰው የሚሸት ህይወት እንዲኖረን ፤ ከምንም በላይ ሴቶች የተሰራንበትን ማንነት እንድንፈትሽ፤ ፈተናችንና ውጣ ውረዳችንን በልባችን ይዘን አንዳችን በአንዳችን ውስጥ መኖር እንድንችል በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ሌላ ዕድል እንደተሰጠን አድርጌ እቆጥረዋለሁ፡፡ መልካም ንባብ!

ትዕግስት ካሳ
ጋዜጠኛ፣ የኮሙዩኒኬሽንና የአድቮኬሲ ባለሙያ

።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።

አብረን
ደራሲ እመቤት መንግስቴ

የእመቤት መንግሥቴ ፅሁፎች ከሰው ልጅ ሕይወት ጋር ቅርብ ናቸው። በየአንዳዳችን ኑሮ ውስጥ በየዕለቱ የሚያጋትጥሙንና፣ ግን ደግሞ ልብ ብለን ሳናጤን የምናልፋቸው እውነታዎች ናቸው። የምትስላቸው ገፅ ባህርያት ሃሳባቸውና ቁመናቸው እንደምናውቃቸው ሰዎች ሥጋ ተላብሰው እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ ከጅምሩ እስከመጨረሻው እንድንከተላቸው ታደርጋለች ።
"በአብሮነት" ድርሳን ውስጥ የምናያቸው ጓደኛሞች የእርስ በእርስ ፍቅር፣ አለሁልሽ የማለት መቆርቆር ፣ በየግል ያላቸው የባህሪ ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለማህበራዊ መደጋገፍ ሊኖራቸው ስለሚገባ እሳቤ ጉልህ የአኗኗር መርሆዎችን በተገቢው ልኬት እያነሳች ለማንኛችንም የሚበጁ የሞራል እሴቶችን አበክራ ታስተላልፋለች። ቆም ብለንም ገፀባህርያቱን እራሳችን ውስጥ በመፈለግ ጥንካሬያችንን እና ድክመታችንን እንድንመረምር ትጋብዘናለች። ለተዋከበ ኑሮ የሚደረግ ሩጫንና ለጋራ መተሳሰብ ሊኖር የሚጋባውን ሚዛናዊ የተረጋጋ የሕይወት ጉዞ በረቀቀ መንገድ አስታርቃ የአብሮነትን ዋጋ ታጎላዋለች። ፅሁፎቿን ላነብ በመቻሌ ክብር ይሰማኛል።

ሰሎሞን ገብሬ
ገጣሚ

--
" ገዥው ስሜት ፍቅር ብቻ ነው "
" Love Is All There Is "

።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።

አብረን
ደራሲ እመቤት መንግስቴ

በአብረን የተሰኘው መጸሐፍ እመቤት መንግስቴ የምታካፍለን በልጅነት ዘመን ከሚያጋጥሙን እና ምልክት ትተው የሚያልፉ እውነታዎችን ነው።

የሰነ ጽሁፍ ችሎታዋን የምታደምቅባቸው ገፅ ባሕርያት ማለትም ሴቶች፣ አብሮ አደጎች እንዲሁም በለጋ እድሜያቸው ውጭ ሃገር ኑሮ የመሰረቱ ሲሆኑ፤ በእለት ኑሮዋቸው ከትውልድ ሃገር ጋር ያላቸወን ትስስር ዘጋቢ በሆነ ውይይትና የአእምሮ ጥያቄ ምልልስ በማቅረብ አንባቢውን የገጠመኞቹ ተካፋይ እንዲሆኑ ትጋብዛለች።

ከአዲስ በሐል እና ኑሮ ጋር ስንጋጭ የሚገጥሙንን የኑሮ ግብግብ በተለይ ብቸኝነትን እና የአእምሮ መታወክን ደራሲዋ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ በደንብ ታሳየዋለች።

መልካም ንባብ

ቪነስ ኢሽዋረን
የኮምዩኒኬሽንና ትርጉም ባለሙያ

09/12/2022

Saturday, September 17 at 5:00pm EAT with Martha H. Kidane, Emebet Mengiste. ከእመቤት ጋር የአዲሱን ሥራዋን ምክንያት አድርገን ስለ መጽሐፏ ለመወያየት ተመልሰናል።

"The bridge between you and the rest of the world is love." Rumi  Give yourself to love.  Happy Friday to all.
09/02/2022

"The bridge between you and the rest of the world is love." Rumi Give yourself to love. Happy Friday to all.

የእግዚአብሄር ጸጋ በዝቶልኝ እነሆ አምስተኛው መጽሃፌ ገበያላይ ዋለ።  የምወዳችሁ እና የማከብራችሁ አንባቢዎቼ ሁሉ በሙሉ መጽሃፌ አማዞን ከዛሬ ቀን ጀምሮ አማዞን ላይ እንደሚገኝ ስነግራችሁ ...
08/25/2022

የእግዚአብሄር ጸጋ በዝቶልኝ እነሆ አምስተኛው መጽሃፌ ገበያላይ ዋለ። የምወዳችሁ እና የማከብራችሁ አንባቢዎቼ ሁሉ በሙሉ መጽሃፌ አማዞን ከዛሬ ቀን ጀምሮ አማዞን ላይ እንደሚገኝ ስነግራችሁ በታላቅ ደስታ ነው። በተጨማሪም መልካም ከተደረገለት ሁሉ መልካም ይጠበቃል እና ከእያንዳንዱ መጽሃፍ ሽያጭ አስር ፐርሰንት ለተፈናቀሉ ወገኖች እንደምለግስ ሳበስር በደስታ ነው። አንብባችሁ አስተያየት አትንፈጉኝ የእድገት በሬ ነውና።

08/08/2022

ገባኝ ቁጥር 2

አንዳንድ ቀን አንድ ትልቅ ነገር ሰርቼ ስጨርስ፣ ወይም ደግሞ ስራ አእምሮ የሚያዞር ነገር ገጥሞኝ ከዋለ እራሴን የማዝናናት የህጻናት ፊልም በማየት ነው።

ብዙ እንዳስብ፣ እንድመራመር ስለማያስገድደኝ፤ ከዛ የበለጠ ግን በደንብ ስለሚያስቀኝና የቀን ውሎዬን ስለሚያስረሳኝ ደስ ብሎኝ አየዋለሁ።

አንዳንድ ቀን ደግሞ በሳቅ ውስጥ የሚገርም ሃሳብ አይና ወይ ጉድ ይሄንንማ ለህጻናት ሳይሆን ማስተማር ለአደግነው ሰወች ነው ለማለት ይዳዳኛል።

ሰሞኑን ሞንስተር ኢንክ(Monster Inc) የተሰኘ የህጻናት ፊልም አየሁ። ያው ስጀምረው እንዲያስቀኝ ወይም ደግሞ ከቀን ውሎዬ እንዲያላቅቀኝ ብዬ ነበር። ግን ይሄ ፊልም ታላቅ ትምህርት አስተምሮ ወይ ጉድ አስብሎኝ ተለያየን።

ሞንስተር ኢንክ የስራ ቦታ ነው። ሞንስትሮችን
የሚቀጥር። ሞንስትሮቹ ደግሞ ስራቸው ሰውን በፍርሃት ወጥሮ መያዝ ነው። ማስፈራራት፣ ማስጨነቅ። ያንበሚያደርጉበት ግዜ ከሚያስፈራሩዋቸው ልጆች የሚገኘውን ኤነርጂ ካንፖኒው እየሸጠ ይከብራል።

ይሄማ የኛ አለም ነው ብዬ አሰብኩ። በማስፈራራት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ። ዜና መስማት ያቆምኩት ለዚህ ነው። በቀን ውስጥ በጥቂቱ አስር የሚያስፈራ ነገር ከዜና እንሰማለን። አስር ነጋዴዎች ደግሞ የፈራነውን ነገር የሚያጠፉ የሚያስታውስ ነገር ሊሸጡልን አሰፍስፈው እየጠበቁ ይቆዩና ወዲያው በማስታወቂያ ጋጋታ ያሳምሙናል።

ወደ ፊልሙ ለደቂቃ ልመልሳችሁ። ሞኒስትር ኢንክ የቀጠረው አንድ ሞንስትር ማስፈራራት አይችልም። የፈለገውን ቢያደርግ ልጆች አይፈሩትም። ቀጣሪዋ ጠርቶ አንተ ማስፈራራት ስለማትችል ከስራ ትባረራለህ አለው። ግን አንድ የመጨረሻ እድል ተሰጠውና፤ ይቺ ልጂ ፈሪ ናት እስዋን ማስፈራራት ካልቻልክ አለቀልህ በቃ ተባለ።

ወደ ልጂትቷ ሄዶ ሊያስፈራራት ሞከረ ግን እስዋ ፍንክች አላለችም። እንደውም መሳቅ ጀመረች። ተስፋ የቆረጠውም ሞንስትር ያለምንም ችግር ያስቃት ጀመር። የሚገርመው ያ ኤነርጂ የሚመዘግበው መሳሪያ፤ ከለቅሶና ከጭንቀት የተሻለ ኢነርጂ ከሳቅዋ እንደሰበሰበ አበሰረ።

አለቃው ጠርቶ እንኳን ደስ አለህ አለው። ከስራ አልተባረረም። ከጭንቀት እና ከፍራቻ ይልቅ የውስጥ ሰላምና ሳቅ የተሻለ ኤነርጂ እንዳለው አስተማረኝ።

አለማችን በሁለት ስሜቶች ትመራለች ይላሉ ተመራማሪዎቹ። አንደኛው ፍረርሃት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ፍቅር ነው። ከፍራቻ፤ ጥላቻ ስግብግብነት ፡ ጭንቀት፣ ቅናት ምቀኝነት እና የመሳሰሉት ሲመነጩ። ከፍቅር ደግሞ ሰላም፣ መተሳሰብ፣ መተጋገዝ፣ መሳቅና፣ መደሰትና የውስጥ ሰላምን የመሰሉት ይመነጫሉ።

ከልጅነት እስከውቀት የማስታውሰው፣ ሰዎች ከፍቅር ይልቅ ፍራቻን እንደሚጠቀሙ ነው። ዋ ለአባትህ እነግራለሁ፣ አያ ጅቦ ይበላሃል፣ እግዚአብሄር ይቆጣል፤ ከፍ ካልን በሗላ ደግሞ፤ ከስራ ቢያስወጡሽስ፤ ትቶሽ ቢሄድስ፤ ብትታመሚስ ወዘተ ወዘተ።

ለህጻናት ልጆች ከተሰራ ፊልም ለዛውም ገንዘብ ሳልከፍል ነፍሴን ለፍራቻ ሳይሆን ለፍቅር ማስገዛትን ተማርኩ። ከመጨነቅ ይልቅ መሳቅን መረጥኩ።

እናንተስ ምን ትላላችሁ?

#እመቤትመንግስቴ #አብረን #ዝምከምልብዬ

https://emebetbooks.com/emebet-mengistes-new-book/
08/05/2022

https://emebetbooks.com/emebet-mengistes-new-book/

Emebet mengiste’s new book -Abren is a beautifully written work of art. Set in Ethiopia, It’s a tale of a childhood friendship, love and loss .The story revolves around eight friends who come into each other’s life in kindergarten and manage to grow old togther. As always her story teaches us ...

07/18/2022

ለምን? ማለት ለምን ነውር ሆነ?

ሳድግ ካማስታውሳቸው ዋነኛ የናቴ መልሶች መካከል ነውር ነው የመጀመሪያውን ቦታ ይወስዳል። እግዚአብሄር ማነው? ብዬ ከጠየኩ መልሱ፤ ስለእግዚአብሄር አትጠይቂ ይሆናል። ለምን? ካልኩ ደግሞ ነውር ነው ይከተላል። ይሄን ልብስ አውልቂ ስትለኝ ለምን? ብዬ እጠይቃለሁ። አሁንም ነውር ነው ይከተላል።

ቀበሌ መሄድ አለብሽም ሊሆን ይችላል፤ ለምን? ካልኩኝ? ሁሉ ሰው ሄዶ አንቺ ስትቀር ነውር ነው ይከተላል። ብዙዎቹ ንግግራችን ላይ እኔም መጠየቄን አላቆምም እስዋም ነውር ነው ማለት አይታክታትም ነበር።

ከፍ እያልኩኝ ስመጣ ግን ነገሮች ተለወጡ። ገና ሳልጠይቃት ለራሴ መልሱን እመልስና ከመጠየቅ እቆጠባለሁ። ለጥያቄዎቹ ሁሉ የመጨረሻው መልስ ነውር ነው እንደሚሆን ጠንቅቄ ስላወኩ የመጠየቅ ፍላጎቴ ጠፋ። እኔም መጠየቅ አቆምኩ።

በቅርብ ቀን አንድ ታሪክ ሳነብ ወደ ልጂነቴ መልሶ ወሰደኝ። እንዲህ ነው። አንድ የቤት እመቤት ለቤተሰብዋ ምግብ ስታበስል ( roast beef) ይሉታል እዚህ አገር። ከተጠቀለለው ስጋ አናት ላይ በደንብ አርጋ አንስታ ከጣለች በሗላ፤ ሌላውን አጥባና ቀምማ ወደ ማብሰያ ድስትዋ ታስገባለች። ይሄንን ደጋግማ የተመለከተች ልጅዋ ታዲያ አንድ ቀን ይሄን መልካም ስጋ እየቆረጥሽ የምትጠይቀው ለምንድነው ብላ ጠየቀች።

እናት በጣም ተገርማ፤ እኔ እንጃ! ለምን እንደሚጣል አላውቅም ግን እናቴ ስታረግ ያየሁት ይሄን ስለሆነ እኔም ያሳየችኝን እያረኩ ነው ብላ መለሰች።

ለምን? ማለት ነውር ነው እንድትጠይቂ ያልተባለችው ልጂ፣ መልስ ለማግኘት የተጨነቀውን መንፈስን ለማርካት ወደ አያትዋ ስልክ ትደውላለች። እናቴ መልካም እራት ሊወጣው የሚችል ስጋ፤ ከስጋው አናት ላይ ቆርጣ ስትጠልቅ ደጋግሜ አየሗት። ለምን ብዬ ስጠይቃት መልስ የላትም። አንቺ ስታደርግ አይታ የውያየችውን እያረገች እንደሆነ ነገረችኝ። አንች ለምንድነው መልካሙ ን ስጋ ቆርጠሽ የጣልሽው ብላ ጠየቀች? አይታየውም የተለየ መልስ የላትም። እናቴ ያሳየችኝን ነው ሳረግ የኖርኩ፣ ለናቴሽም ያስተማርኳት ያንን ነው ብላ መለሰች።

ጀግኒት ጥማትዋን ለማርካት ወደ ቅድም አያትዋ ስትደውል። ቅድማያት በመገረም ከሳቁ በሗላ፤ እኔ እኮ ቆርጬ የሚጥለው የነበረኝ ድስት በጣም አነስተኛ ስለነበረ እና ሙሉውን ስጋ መክተት ስለማይችል ነው ብለዋት አረፉ። ለምን ብሎ ካለመጠየቅ ስንት ስጋ ባከነ።

በጣም እየገረመኝ እነኝህ መሐል ላይ ያሉ ሁለት እናቶች ማሰብ ጀመርኩ። ምናልባት እንደኔ አትጠይቁ፣ እየተተባሉ አድገው ይሆን? እንደኔ መጠየቅ ታክቶዋቸው ወይም መልሱ ምን እንደሚሆን በልባቸው ተገንዝበው መጠየቅ አቁመው ይሆን?

በህይወቴ ውስጥ ስላሳለፍኳቸው ብዙ ነገሮች ማሰብ ጀመርኩ። በስማም!! ለምን? ግን ለምን ነውር ሆነ? ለምን ብሎ የጠየቀ ሰው መልስ ያገኛል። መልስ ካላገኘ ደግሞ መመራመርና የራሱን መልስ ወደ መፈለግ ያመራል። ለምን ከለከሉን? ለምን መልስ ነፈጉን? ለምን? ለምን? ለምን?

አትጠይቁኝ የሚል ማህበረሰብ፤ ሳይጠይቅ የሚከተል ዜጋ ያፈራል። በጣም በብዙ ፓውንድ የሚቆጠር ስጋን ከመጣል አንስቶ፣ መፈለግ ያቆመ እውነት ያልራበው፣ የሰጡትን ብቻ የሚቀበል፣ ግደል ሲባል የሚገ፣ ለምን ብሎ የማይጠይቅ ዜጋን ያፈራል።

ለምን፣ ነውር አይደለም። መሆንም የለበትም። ለምን የሁላችንም ጥያቄ መሆን አለበት። ለምን የመብትም የእውቀትም፣ የእውነትም ጥያቄ ነውና መጠየቅ አለበት። አሁን ሲገባኝ። ምናልባት ነውር የሆነው ብዙዎች መልሱን ስለማያውቁት ነው።

መልሱን ለማናውቀው ጥያቄ ነውር ነው ብለን በር ከመዝጋት ይልቅ አብረን መልሱን እንፈልግ ማለት መፍትሄ ይሆን?

#እመቤትመንግስቴ #ዝምከምልብዬ #አብረን #በቃ

06/29/2022

ሰሞኑን የከተብኩት፣አስተያየት መስጠት ይቻላል።

ዘር ስጡኝ

ሳንሰማማ ተነጋግረን
ወይ ሳንነጋገርው አምቀን
በቃላት ግርግር ጋጋታ
ወይ በኩርፊያ ዝምታ
ነበልባ እሳት ከውስጣችን ሲነድ
ለጥላቻ ረመጥ ፍቅር ስንማግድ
ፍቅር ሲርቅ ሲሸሽ ከስጣችን
ለጥላቻ ሲገዛ ነፍሳችን
አላየንም አልሰማንም ብለን
ጥላቻን ዘርተን፤ እሱኑ አበቀልን

ዘር ስጡኝ እባካችሁ
ፍቅር ሲሄድ ሲርቅ፣ ዘግናችሁ ያስቀራችሁ
መነጋገር፣ መደማመጥ፣ መከባበር፣ ያላመለጣችሁ
ዝምታና፣ ኩርፊ በቀል፣ ያልገዛችሁ
ለኔም አበድሩኝ፣ መልሼ እሱን ልዝራ
ይበቅል ከሆነ፣ ለነፍስን የሚያራራ

ዘር ስጡኝ ባካችሁ፣ ፍቅር የሚያበቅል
ልዝራው ደጋግሜ ነፍሴ እልል እድትል
የዘሩትን ማጭድ ከሆነ የተጻፈው
ፍቅርን ስጡኝ ልዝራ መልሼ ላብቅለው።

#በቃ #ዝምከምልብዬ #አብረን #እመቤትመንግስቴ

https://youtu.be/BVwjkCbMVLE
05/25/2022

https://youtu.be/BVwjkCbMVLE

ፓርክ ጉብኝት ከዲያስፖራዋ ደራሲ፣ ገጣሚ፣ የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅና አሰልጣኝ እመቤት መንግስቴ ጋር

05/19/2022

ስጦታዬ

ከጥቂት አመታት በፊት አንድ ወዳጄ ደወለችልኝ። ከልጂነት ጀምሮ የምንተዋወቅ ስለሆንን፤ ከአቆምንበት መቀጠል ብዙም አያስቸግረንምና ለረጂም ሰአት አወራን። ጓደኛዬ በጨዋታ መካከል ጤናዋ ጥሩ እንዳልሆነ ካጫወተችኝ በሗላ ብንገናኝ መልካም እንደሚሆን ተነጋገሩ ስልኩን ዘጋን።

የምንኖረው የተለያየ ከተማ ስለሆነና የኑሮ ጫና እድል አልሰጥ ብሎኝ፤ ቆይ በዚህኛው ሳምንት፣ ቆይ በሚቀጥሉ ወር እያልኩ ሳመነታታ ሄጄ ሳላያት አመት ሞላ።

በየግዜ በስልክ ብናወራም፣ በርቀትም ቢሆን የተቻለኝን ሁሉ ባደርግላትም፣ አይዞሽ በርቺ የሚል ድጋፌ ባይለያትም ሄጄ ለማየት በፍጽም አልሞላልኝም።

ከአመት በሗላ አንድ ቀን ከዶክተር ቆጠሮ ስትመለስ፣ እንደተለመደው ደወልኩላት። ዛሬም አንደወትሮዋ እየሳቀች አወራችኝ። ሰላም እንደሆነች የውስጥዋ ሰላም ሙሉ እነደሆነ ከነገረችኝ በሗላ "ዶክተርዋ በምድር ላይ ያላት ግዜ ከስድስት ወር እንደማይበልጥ እንደነገራት እየሳቀች ነገረችኝ"።

እኔ የምይዘውን የምጨብጠውን አጣሁ። እሷ ግን ፈርጠም ብላ። "የመጨረሻውን ቀኖች ስቆዝም ማሳለፍ አልፈልግም" "ስስቅ፣ ስጫወት፣ ፈጣሪዬን እዚህ ምድር ላይ ለሰጠኝ ሰአት ሳመሰግን ነው እንጂ" "የምታለቅሺ እና የምትቆዝሚ ከሆነ አልፈልግሽም አለችኝ።"

ትንሽ አጉረመረምኩ፤ ቢሆንም ግን ፈቃድዋን ማክበር ነበረብኝ እና ምላርግ ብዬ ጠየኩ።

እሱ በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው! ነይና እንተያይ። "እንሰነባበት" አንድ ሙሉ ቀን ላንቺ ብቻ እሰጥሻለሁ። የቀረኝን ሰአት ከምወዳቸው ሰወች ጋር ብቻ ለማሳለፍ ወስኛለሁ። ለማልቀስ እና ለመደበር ሳይሆን ለመሳቅ እና በደስታ ለመሰነባበት! አንቺ ደግሞ ከመረጥኳቸው ሰወች የመጀመሪያዋ ነሽ። ስለዚህ ሳታወላውይ ነይ አለችኝ።

እኔም ምንም ሳላመነታ ነይ ባለችኝ ቀን ደረስኩ። አንድ ሙሉ ቀን አብረን አሳለፍን ብዙ ሳቅን፣ በጥቂቱም አለቀስን። አንዳንድ መደረግ ስላለባቸው ነገሮች ነገረችኝ። ለመሄድ ከመዘጋጀትዋ ባሻገር ማንም እንዳይቸገር በደንብ እየተዘጋጀች እንደሆነ አየሁ።

የተፈቀደልኝ ቀን ከማለቁ በፊት አንድ የገረመኝን ነገር ነገረችኝ። "በህይወቴ ሙሉ አንድም እኔ የመረጥኩት ነገር ሆኖ አያውቅም አለችኝ። እግዚአብሔር ለኔ በመረጠልኝ ግን ተደስቼ ኖርኩኝ" አሁንም የመረጠልኝ ጽዋ ይሄ በመሆኑ በደስታ ተቀበልኩት ብላ ዝም አለች።

እጂግ በጣም ስለገረመኝ ምን ማለትዋ እንደሆነ ጠየኩ። በልጂነቴ እኔ መነኩሴ (ነን )መሆን ነበር ፍላጎቴ፤ ቤተሰብ ከዛ አላቀቁኝ። ከፍ ስል እኔ መማር የፈለኩት ነርስነት ነበር፤ ግን የተማርኩት አካውንቲንግ ሆነ። ላገባ የፈለኩት እገሌን ነበር፣ የገባሁ ግን ሌላ ሆነ። ብላ ብዙ በህይወትዋ ውስጥ ስለተፈጠሩ ነገሮች አጫወተችኝ።

ደገመችና እኔ የመረጥኩት ባይሆንም ፈጣሪዬ በመረጠልኝ እጂግ ተደስቼ ኖርኩ። የአሁኑም የተለየ አይሆንም አለችኝ።

በጥንካሬዋ ቀናሁ፣ ከምክርዋ በረከትን አገኘሁ፣ መቀበልን የመሰለ ታላቅ ውብ ስጦታን ሰጠችኝ። ለምን እኔ ሳይሆን፣ እንደፈቃድህን ተማርኩ። እንባዬ በአይኔ መሙላት ሲጀምር በቃ ሂጂ ብላ አባረረችኝ። ደግሜ ላላያት ተሰናብቼ ወጣሁ።

ወደቤቴ እየነዳሁ ትንሹንም ትልቁንም ስጦታወቼን አሰብኳቸው። እኔም ህይወት ውስጥ የተሰጡኝ ድንቅ ስጦታወች ግን እኔ እንደስጦታ ያላየሗቸው ውብ ነገሮች አገኘሁ። እንደ ስጦታ ተቀብያቸው ቢሆንም ኖሮ እንዴት ደስ የሚል ህይወት ይኖረኝ እንደነበር አሰብኩ። ቢሆንም አሁንም አልረፈደ ም ብዬ ተጽናናሁ።

አንድ ወቅት ላይ ባለቤቴ እጂግ የሚያምር ውድ ስጦታ ገዝቶ ሰጠኝ። በርግጠኝነት ያንን ለኔ ለመግዛት ብዙ ተጨንቆዋል። ብዙ ሰአትና ገንዘብም አጥፍቶዋል። እኔ ግን የፈለኩት ሌላ ነገር ስለነበር፣ ምን ያክል እንዳናደደኝ እና ምን ያክል እሱንም እንዳስቀየምኩት ማሰብ ጀመርኩ። ብዙዎቹን ፈጣሪ ተጠቦ እና ተጨንቆ የመረጠልኝን ስጦታወች እኔ የፈለኩት እሱን አልነበረም ብዬ እንዳበላሸሗቸውም ተሰማኝ።

ከዛም ስለ እያንዳንዱ የምድር ስጦታም አሰብኩ። አምላክ የሚሰጠንን እያንዳንድን ስጦታዎች በደስታ መቀበል ስንችል የተሻለ ህይወት መኖር እንደምንችልም ተረዳሁ። ወደ ህይወታችን የሚመጡ ሰወች፣ ልጆቻችን፣ ስራችንን ጨምሮ፤ እንደ ስጦታ ተቀብለን መደሰት እንችላለን! እኛ ያሰብነው ባይሆንም በውበትና በጥሞና የተመረጠልን ነውና።

የተሰናበትኳትን ጋደኛይን እያሰብኩና እንባዬን እያበስኩ፤ ለካስ ምድር ላይ መኖራችንም ታላቅ ስጦታ ነው። የተሰጠንን ሰአት ጨርሰን መሄዳችን ጭምርብዬ አሰብኩ።

ዝም ከምል ብዬ

#እመቤትመንግስቴ #አብረ #ዝምከምልብዬ

04/07/2022

አለሜ ነሽ አለኝ
እናተ ፍረዱኝ

ልክስክስ ናት አለም
ለማንም አትሆንም

ሰጥታ ትነፍጋለች
ደስታን ታቅባለች

ብሎ እየሰበከ

አለሜ ነሽ አለኝ
አለም ብሆንለት
ደስ አሰኘው ይሆን
ወይስ እከፋበት

#ዝምከምልብዬ

03/08/2022

ለእህቴ

ለአንቺ ለውዲቱ
እንጨትና ቅጠል ለተሸከምሺቱ
አይዞሽ እናት አለም
ቀን ያልፋል ግድ የለም

እናም አትድፊ አንገትሽን
ለአለም አይቶልሻል ብርቱ መሆንሽን
በተሸከምሽው ስር ሃያል ተስፋ እንዳዘልሽ
ከቅጠሎቹ ስር ብርሃን እንዳገኘሽ
እህቴ እናት አለም
ነገ ሌላ ቀን ነው ማይለወጥ የለም።

ለእቴ ላንቺ ለዶክተርዋ
በርችልን አንችዋ
መድሃኒት ነው እጂሽ
ተስፋ ነው ፈገግታሽ
አበርቺ ነው ምክርሽ

እናማ እህት አለም
ለአንቺ የገባሽ ለነሱ ያልታያቸው
ያንቺ ህልም ለነሱ ቅዠት ሆኖባቸው
እንቅፋት ሊሆኑሽ
መንገድ ሊዘጉብሽ
ቢከጂል ልባቸው
ተይው እናት አለም ጨርሶ አትስሚያቸው
የውስጥሽን መብራት እንዳታጨልሚ
ሁል ግዜ ለምልሚ።

ለእህቴ ላንቺ ለመምህርዋ
ታጋሽ አገልጋይዋ
እውቀት አካፋይዋ
አምሮ አናጭዋ
ነገ ተተኪ ትውልድ ገንቢ ነሽ
እውነት ያለ ውስጥሽ
በርችልን እቴዋ እንዳትቆርጭ ተስፋ
የቆምሽለት ብርሃንሽ አይጥፋ።

ለቤት እመቤቷ ለአንቺ ለእህቴ
ታላቅ ነው ክብረቴ
እናትነት መርጠሽ
ለልጆቼ ብለሽ
ለዋልሽው ከቤትሽ
የአነጽሻቸው ልጆች ምስጋና ይድረስሽ
ይታይ ብርሃንሽ።
ያጎረሽበትን አይዞህ ያልሽበትን
ታሪክ ይዘክርሽ

ለእህቴ ለአንቺ ለውቢቱ
አገር መሪይቱ
ማስተዋልን ለሞላሽ
በሙያሽ ለኮራሽ
እህቶችን ሁሉ
እኔም እችላለሁ
ላገሬ እሰራለሁ
ለወገን እጎማለሁ
ብለው እንዲያስቡ
በር ለከፈትሽው
ፈር ቀዳጂ ለሆንሽው
ምስጋናዬ ይድረስሽ
ከሁላችንም ዘንድ በርቶዋል ብርሃንሽ

የለእህቴ በባእድ አገር ላለሽው
የስራ ክብደቱ
የሰዉም ክፋቱ
ምንም ሳያግርሽ
ለወገን ለደረስሽ
እህትሽን ላስተማርሽ
ወንድምሽን ላቋቋምሽ
ከእንባሽ ስር እየሳቅሽ ብዙውን ላሳለፍሽ
ላንችም ለውዲቷ ምስጋና ይድረስሽ።

ባውቅም ባላውቃችሁ
በአለም ዙሪያ ሁሉ ለተፈጠራችሁ
እንስት እህቶቼ
እንኳን ለሴቶች ቀን በሰላም
ደረሳችሁ።

እንደወረደ የሚባል ግጥም
15 ደቂቃ ቀኑን ለማክበር

ተጻፈ 03/08/2021

ለአባይ ግድብ በስጦታ ያበረከትኩት መጸሃፍ አሁን አዲስ አበባ ከተማ በነዚህ ቦታዎች  ይገኛል።  አንድ አንድ በማንሳት አባይን ደግፉ። ጃፋር _ ለገሃርና ሜክሲኮ ሰዓዳ መጻሕፍት _ ለገሃርዓይ...
02/04/2022

ለአባይ ግድብ በስጦታ ያበረከትኩት መጸሃፍ አሁን አዲስ አበባ ከተማ በነዚህ ቦታዎች ይገኛል። አንድ አንድ በማንሳት አባይን ደግፉ።

ጃፋር _ ለገሃርና ሜክሲኮ
ሰዓዳ መጻሕፍት _ ለገሃር
ዓይናለም _ ብሔራዊ
ሀሁ መጻሕፍት ሜክሲኮ
እነሆ መጻሕፍት አራት ኪሎ
ጌታቸው ጊዮርጊስ
አስቻለው አውቶብስ ተራ
ሊትማን ጥቁር አምበሳ
አዳነ መጻሕፍት አራት ኪሎ
አለ።

መልካም ንባብ።

Sasha Alyson 🌍🌏🌎 Karma Colonialism () Tweeted: Do you live in Ethiopia?Are you from Ethiopia?The Guardian wants to hear ...
11/12/2021

Sasha Alyson 🌍🌏🌎 Karma Colonialism () Tweeted: Do you live in Ethiopia?
Are you from Ethiopia?

The Guardian wants to hear about your recent experiences and how you view events there.

They offer several ways to contact them, to preserve anonymity if you wish.
https://t.co/KhJprPndqJ
https://twitter.com/TrojanAid/status/1457564535859122178?s=20

We would like to hear from people in Ethiopia and those who are part of the diaspora on the situation in the country

11/03/2021

ጩሂ፣ ጩሂ፣ አለኝ
እንኳንስ የሚያስጮህ ሚጣራ ድምጽ የለኝ
አልቅሽ፣ አልቅሽ፣ አለኝ የት ሄጄ ላልቅሰው
እምነቴን ሲያሳጣኝ ሰው እየበላ ሰው
ግደይ፣ ግደይ አለኝ ማንን ልግደልበት
ወንጀለኛ እንጂ አዳኝ በሌለበት
ፍረጂ፣ ፍረጂ፣ አለኝ ፍርድ መች አውቄ
ተፈተንኩኝ እንጂ ፈጣሪን ጠብቄ

ፈራጂም አንተው ነህ
መከታም አንተው ነህ
አዳኝም አንተውነህ
ብለን እያመንህ
ፈጣሪ ለህዝብህ
ምነው መዘግየትህ

#ዝምከምልብዬ #አብረን

Address

4325 Firs Avenue Suite # 3083
Tucker, GA
30084

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when ABREN MEDIA & Entertainment posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Business

Send a message to ABREN MEDIA & Entertainment:

Share


Other Media/News Companies in Tucker

Show All