05/29/2024
Oromia Times
በሀገራችን በቤቱ መብራት የማይጠፋበት ብቸኛው ወጣት
*********************
ወጣት ፈዴሳ ሹማ በኃይል አማራጭ ዘርፍ አብዮት ይፈጥራል ተብሎ የታመነበት መሣሪያ የፈጠራ ባለቤት ነው፡፡
ፈዴሳ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት የተዘጋጀው ልዩ የክረምት ወራት የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ሀሳቦች ማበልፀጊያ መርሐ ግብር ካሰባሰባቸው ወጣቶች አንዱ ነው።
ፈዴሳ ሹማ ተወልዶ ያደገው በቄለም ወለጋ ሲሆን፣ በከተማው ውስጥ በኤሌክትሪክ ጥገና ሙያው ይታወቃል፡፡ ይህን የኤሌክትሪክ ጥገና ሥራውን የመብራት መጥፋት እና መቆራረጥ ብዙ ጊዜ አስተጓጉሎበታል።
"ችግር ብልሃትን ይወልዳል" እንዲሉ ወጣቱ ሥራውን በተደጋጋሚ ላስተጓጎለበት ችግር መላ መዘየድ እንዳለበት አሰበ፤ አስቦም ወደ ተግባር ገባ።
ከብዙ ጥረት በኋላ አንድ ጊዜ ቻርጅ ተደርጎ እስከ አንድ ዓመት ድረስ አገልግሎት መስጠት የሚችል ቴክኖሎጂ እውን አደረገ።
ፈዴሳ በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በሚመራው ልዩ የክረምት ወራት የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ሀሳቦች ማበልፀጊያ መርሐ ግብር ተሳትፎው ባገኘው ስልጠና እና ሙያዊ ድጋፍም ቴክኖሎጂውን ይበልጥ አዘምኖ መሥራት ችሏል።
ቴክኖሎጂው የመብራት አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ ለሞባይል፣ ለቴሌቭዥን፣ ለፍሪጅ እና የትኛውንም ዓይነት የኤሌክትሮኒክስ መጠቀሚያዎችን ቻርጅ የሚያደርግ፣ የሚያንቀሳቅስ እና በገመድ እና ገመድ አልባ ቴክኖሎጂ መጠቀም እንዲቻል ተደርጎ የተሠራ ነው።
አንዴ የያዘውን ኃይል ደጋግሞ እያደሰ (recycling) ራሱን ቻርጅ ከማድረግ አልፎ ለረዥም ጊዜ ኃይል ማመንጨት የሚችለው ይህ ቴክኖሎጂ በሀገራችን ብቻ ሣይሆን ምን አልባትም በዓለማችን ላይ በኃይል አማራጭ ዘርፍ አብዮት መፍጠር እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል።
ከ300 ዋት ጀምሮ እንደ ተጠቃሚው አቅም እና ፍላጎት የሚዘጋጀው ይህ ድምፅ አልባ ጄኔሬተር አንድ ጊዜ ቻርጅ ተደርጎ ከአንድ ዓመት በላይ አገልግሎት መስጠት እንደሚችል ነው ወጣቱ ያረጋገጠው።
በዚህም ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በሀገራችን በቤቱ መብራት የማይጠፋበት ብቸኛው ሰው መሆኑን ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ የሚያመላክተው፡፡
አሁን ላይ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ወጣቱ የራሱን ኩባንያ የሚከፍትበትን እና ቴክኖሎጂው በስፋት ተመርቶ ለህብረተሰቡ ማድረስ የሚቻልበትን ሁኔታ ላይ እየሠራ ይገኛል ተብሏል።