08/27/2023
ከአሁን በኋላ በካድሬነት ሳይሆን ...
| የትምህርት ቤቶች ርዕሳነ መምህራን ከአሁን በኋላ በካድሬነት ሳይሆን በብቃታቸው ብቻ እንደሚመረጡ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ይህንን ያለው ነሐሴ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ 30ኛውን ዓለም አቀፍ የትምህርት ጉባዔ ባካሄደበት ወቅት ነው፡፡
የትምህርት ሚኒስትር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ምን አሉ ?
ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ፦
" የትምህርት ቤቶች አስተዳዳሪዎች ከአሁን በኋላ የሚመረጡት በካድሬነት ሳይሆን፣ ባላቸው ብቃትና ችሎታቸው ላይ መሠረት ተደርጎ ይሆናል።
በዚህ መሠረት በአገር አቀፍ ደረጃ በብቃታቸውና በችሎታቸው የተመዘኑ 1,600 የትምህርት አስተዳዳሪዎች ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል። ይህ ዓይነቱ አሠራር ቀጣይነት ይኖረዋል።
የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ከማሳደግ ሥራ በተጨማሪ የመምህራንና ርዕሳነ መምህራን ብቃትና ችሎታ ማጎልበት ትኩረት ተሰጥቶበታል፡፡
ትኩረት ካገኙ መሠረታዊ ጉዳዮች ትምህርት ቤቶችን በግብዓትና በጥራት ከማሻሻል ባሻገር ክህሎት፣ ብቃትና ችሎታ ባላቸው ርዕሳነ መምህራን እንዲተዳደሩ ማድረግ ትልቁን ድርሻ ይይዛል።
የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ከማሻሻል በተጨማሪ በዕውቀት ተማሪዎቻቸውን ተወዳዳሪ ማድረግ የሚችሉ መምህራንን ማብቃት ከተያዙ ግቦች መካከል አንዱ ነው።
ባለፉት 30 ዓመታት የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ጥራት ወርዷል ፤ በኑሮ ለተሻሉ ደግሞ የግል ትምህርት ቤቶች የሚማሩበት ሥርዓት ተዘርግቷል።
ይህ ዓይነት አካሄድ በዜጎች መካከል በኑሮ ደረጃ ከተፈጠሩ ልዩነቶች አልፎ በትምህርት ዘርፍ ላይ መታየቱ ትልቅ ክስረት ነው። ይህ አካሄድ በአገር አቀፍ ደረጃ አደገኛ ሁኔታዎች የሚፈጥር ነው ፤ በየትኛውም የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች በገንዘብ ዕጦት ሳቢያ የትምህርት ጥራት ሊጓደልባቸው አይገባም።
ትምህርት የአገር የሉዓላዊነት እሴት መለኪያ ነው ፤ በዚህ ጉዳይ ለዓመታት የተቀለደበት ዘርፍ ነው አሁን እርስ በርስ መነጋገር የማይቻልበት ሁኔታ ላይ መደረሱ የችግሩ ማሳያ ነው።
የትምህርት ዘርፍ መሠረታዊ መርሆዎች ሁለት ናቸው ፤ ዜጎች በብሔራቸውና በሃይማኖታቸው ሳይታዩ እኩል ጥራት ያለው ትምህርት የማግኘት መብታቸውን ማረጋገጥ አንደኛው ነው።
የትኛውም የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች ከሁሉም እኩል ተወዳዳሪና ተፎካካሪ የሚሆኑበትን የትምህርት ሥርዓት በመዘርጋት፣ አሁን ያለውን የኢፍትሐዊነት ችግር በዘላቂነት መፍታት ይቻላል።
በኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፉ ከአሥር ዓመታት በኋላ ትምህርት ቤቶች እንደ አሁኑ የፀብ (የረብሻ) መፍለቂያ ሳይሆኑ የመወዳደሪያና የብቃት ማጎልበቻ ይሆናሉ፡፡
ከዚህ በኋላ እንደ ከዚህ ቀደሙ ዲግሪ እንደ ከረሜላ የሚታደልበትን አሠራር አስቀርቶ፣ በብቃት እና በችሎታ ብቻ ዜጎች ማዕረግ የሚያገኙበት ሥርዓት በዘላቂነት ይዘረጋል። "
G.T