01/04/2025
ግብፅ ወታደሮቿን በአውሮፕላንና በመርከብ ወደሱማሊያ ለመላክ ዝግጅቷን ማጠናቀቋን ዘናሽናል ዘግቧል
እንደዘገባው እነዚህን ወታደሮች የምትልከው በአዲሱ የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ሀይል ውስጥ ለማካተት ነው፡፡
ግብፅ ወታደሮቿን ወደሱማሊያ የምትልክው በሱማሊያ ጥያቄ መሰረት መሆኑን ያወሳው ዘገባው ቀደም ሲል በርካታ የጦር መሳሪያዎችን ወደዚያው መላኳን ጠቅሷል፡፡ በዚህ ሳምንት በተከናወነው የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ በሱማሊያ ውስጥ አዲስ ሰላም አስከባሪ ሀይል እንዲሰማራ የተወሰነ መሆኑን የገለፀው ዘገባው ይህን ተከትሎ የግብፅ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የግብፅ ወታደሮች በአዲሱ ሀይል ውስጥ እንደሚካተቱ ማስታወቁን ጠቅሷል፡፡
በፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ መሰረት በአዲሱ ሰላም አስከባሪ ሀይል ውስጥ አስራ አንድ ሺ ወታደሮች እንደሚካተቱ መገለፁ ይታወሳል፡፡
በናሽናል ጋዜጣ እንደዘገበው ግብፅ ከዚህ ውስጥ ሀያ አምስት ፐርሰንቱን ለመሸፈን ዝግጅት እያደረገች ትገኛለች፡፡ እነዚህ ወታደሮችም በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ በአውሮፕላንና በመርከብ ተጭነው ሞቃዲሾ ይደርሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዘገባው አስረድቷል፡፡