10/04/2024
https://www.facebook.com/100064792596360/posts/818933260276420/?app=fbl
ሚያዝያ1 /2016ዓ.ም
================
የጉራጌ ዞን አስተዳደር ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1445ኛ ጊዜ ለሚከበረው የኢድ አል-ፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ የሚል መልዕክት አስተላለፈ፡፡
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በዓሉን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት መንግስት የሀገራችን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ እየወሰዳቸው በሚገኙ እርምጃዎች የሙስሊሙ ማህበረሰብ ተሳትፎ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በየደረጃው የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ የልማት ሰራዎች ከግብ ለማድረስ ሙስሊሙ ማህበረሰብ እንደ ትላንቱ ከሌሎች ወንድምና እህት ህዝብ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።
ሙስሊሙ ማህበረሰብ ለ1 ወር ያህል ሀገር ሰላም እንድትሆን፣ የበረከት ዝናብ እንዲዘንብ፣ ምድር እንድትለመልም፣ የሰው ልጅ መልካም እንዲሆን በፆምና በፀሎት ያሳየው መልካም ስነ-ምግባር፣ በቀጣይም በሀገራዊ አንድነትና ሰላም ላይ መድገም እንደሚኖርበት ተናግረዋል፡፡
የሀገሪቱን በተለይም የዞኑ ሰላምና የህዝቡ እንድነት በዘላቂነት ለመጠበቅ ህዝበ ሙስሊሙ ከሌሎች እምነት ተከታይ ወገኖቹ ጋር በመሆን የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት አስገንዝበዋል አቶ ላጫ፡፡
የሀይማኖት ተቋማት በሀገር ሰላምና ልማት ላይ ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የሀይማኖት አባቶች ህብረተሰቡን ለማስተማርና ለማነጽ የሚያደርጉት ጥረት አጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
የሀገራችን ህዝቦች ከሚለያዩበት ይልቅ አንድ የሚያደርጋቸውና የሚያቀራርባቸው እንዲሁም እርስ በእርስ የተዛመዱበት በርካታ እሴቶች እንዳላቸው የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው የጎዳና ላይ ኢፍጣር አንዱ ማሳያ እንደሆነም አስገንዝበዋል።
ህዝበ ሙስሊሙ በሀይማኖት፣ በብሔርና በዘር ሳይከፋፈል የተራቡትን በመመገብ፣ የታረዙትን በማልበስ፣ ያጡትን በመለገስ፣ አቅመ ደካሞችን በማገዝ የኢድ አልፈጥር በዓልን ማክበር ይኖርበታል ብለዋል።
ወጣቶች ከአባቶች የወረሷቸው የአብሮነት፣ የመረዳዳትና የመቻቻል እሴቶች በመተግበር አርአያነት ያለው ተግባር መፈጸም እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል።
በመጨረሻም አቶ ላጫ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ለ1445ኛዉ የኢድ አል ፈጥር በዓል እንኳን አደረሳችሁ በማለት በዓሉ የሠላም፣ የፍቅርና የጤና እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
መልካም የኢድ አል ፈጥር በዓል!!!
ኢድ ሙባረክ!!