20/04/2024
❣️ ዲያቆን መኩሪያ ጉግሣ
በሺህ የሚቆጠሩ መዝሙራትን ለኦርቶዶክስ ዘማሪያን ያበረከተ
[ በወፍ በረር ... ]
| ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ከዝማሬ ጀርባ የነበረውና በሺህ የሚቆጠሩ መዝሙራትን ለኦርቶዶክስ ዘማሪያን ያበረከተው ዲያቆን መኩሪያ ጉግሣ ፣ ስሙ ሥራውና ጸጋው በስቲከርና በከቭር ላይ ብቻ ተለጥፎ ይኖር ከነበረበት አገልግሎት ወጥቶ ወደ አደባባይ ብቅ ብሏል !!
ለዝማሪ ቴዎድሮስ ዮሴፍ፣ ቀሲስ ምንዳዬ ብርሃኑ፣ ዳግማዊ ደርቤ ፣ ቸርነት ሰናይ ፣ ፍቃዱ አማረ ፣ አቤል መክብብ ፣ ገብረ ዮሐንስ ገብረ ፃድቅ ፣ እስጢፋኖስ ሣህሌ ፣ ኢዮብ ዘለቃ፣ ለምለም ከበደ ፣ ፀዳለ ጎበዜ አዲስ ለማ ፣ ህይወት ተፈሪ፣ የትምወርቅ ሙላት፣ ቅድስት ምትኩ ፣ ትዕግስት ስለሺ፣ ትንቢት ቦጋለ ... በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዘማሪያን መዝሙሮችን ደርሷል ...
ደራሲው የብርሃን ሽግግር እና ዝማሬ ተዋህዶ ቁጥር 1 የተሰኙ ሁለት የግጥም መጽሐፍትን ያሳተመ ሲሆን በቅርቡም ለሦስተኛ መድብሉ እየተዘጋጀ መሆኑን አውቀናል።
ዲያቆን መኩሪያ በዘፈኑ ዓለም ለሚታወቁ ባለሙያዎችም ሥራዎችን እንዳበረከተ ሰምተናል ። አፈሩ ይቅለላቸውና ለጥላሁን ገሠሠና ለታምራት ሞላ ሙሉ ሥራ መስራት ተጀምሮ በጤና ችግር ምክንያት ሳይጠናቀቅ እንደቀረ ዲያቆን መኩሪያ ነግሮናል ።
በአሜሪካ ቨርጂንያ ለሚገኝ የልደታ ቤተክርስቲያን ማሰሪያ እንዲውል ለአንጋፋው መሐሙድ አህመድ ፣ በዛወርቅ አስፋውና አለም ከበደ ሙሉ አልበም ሰርቶ አበርክቷል ።
የዘፈን ህይወታቸውን አቁመው በንስሃ ህይወት ላሉት አቦነሽ አድነው ፣ ማርታ አሻጋሪና በዛወርቅ አስፋው ስራዎቹን አበርክቷል።
በቅርቡ ራሱ ደራሲው በከፈተው በዜማ ሰማያት የተለቀቅውን የዘማሪት በዛወርቅ አስፋውን " ፈራሁ " የሚለውን ዝማሬ ለህዝብ አቅርቦም በሚሊዮኖች እየተደመጠ ይገኛል ።
በዛወርቅ አስፋው አስቀድማ የሰራችውን "ይቅርታ" የሚለው ዝማሬም የዲያቆን መኩሪያ ድርሰት ነበር ...
አብነት በአዴ ሜዳና አለሙ ሜዳ መሃል ተወልዶ ከወላጆቹ ጋር ወደ አየር ጤና በመሄድ በአየር ጤና ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን ያገለግል የነበረ ሲሆን ዛሬ ኑሮውን ካባለቤቱና ከሦስት ልጆቹ ጋር በአሜሪካ ቨርጂንያ ካደረገ አሥራ አምስት ዓመታት ተቆጥሯል !!
ዲያቆን መኩሪያ የደራሲ ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) ጎረቤት እንደነበረና የገጣሚነት መንፈሳቸው አርፎብኝ ይሆን? እያለ ቢጠይቅም ፣ ግጥምን ግን ከቤተ መቅደስ የግእዝ ጸሎቶች እንደተማረ በመደጋገም ይናገራል !!