10/09/2022
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ የተከበሩ አቶ አክሊሉ ለማ የ2015 ዓ/ም አዲስ ዓመት በዓል በማስመልከት የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላለፉ፡፡
ለመላው ወላይታ ብሔረሰብና ለሀገራችን ህዝቦች እንኳን ለኢትዮጵያዊያን የዘመን መለወጫ አዲሱ አመት በዓል በሠላም አደረሳችሁ!አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የጤናና የብልጽግና እንዲሆን በራሴና በወላይታ ዞን አስተዳደር ስም መልካም ምኞቴን እገልፃለሁ።
አገራችን ኢትዮጵያ የብዝሃ ብሔር፣ ኃይማኖት፣ ባህልና ቋንቋ ሀገር ስትሆን ሁሉም ብሔረሰቦች፣ ኃይማኖቶች፣ ባህሎችና ቋንቋዎች ለዘመናት ተቻችለው የሚኖሩባት የሁሉ እናት የሆነች ሀገር ነች።
ሆኖም የኢትዮጵያ ጠላት ሆኖ ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ሲያስተዳድራት የቆየው የጁንታው ቡድን በ"ከፋፍለህ ግዛ" የቅኝ ገዢዎች እሳቤ እርስ በርሳችን እንድንከፋፈልና እንድንናቆር አድርጎን ቆይቷል።
ከዛሬ አራት ዓመት በፊትም በህዝብ ማዕበል ሥልጣኑን ከለቀቀ በኋላ "እኔ የማልመራት ኢትዮጵያ ትፍረስ" በሚል አስተሳሰብ የአገራችን ምልክት የሆነውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ በመውጋት መንግስት ተገዶ ወደ ጦርነት እንዲገባ አድርጓል።
በዚህም ጦርነት ጁንታው ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ከሆኑ ሀገራትና ኢትየጵያን እንደፈለግን ካላሾርናት ከሚሉ ምዕራባውያን ጋር በማበር በኢኮኖሚና በሚዲያ የከፈቱብን ወረራ በመመከት የሀገራችን አንድነትና ሉአላዊነትን በማስስከበር በፈተናዎች ውስጥ ሆነንም አኩሪ የልማት ድሎችን ማስመዝገብ ችለናል።
ያለጦርነት መኖር የማይችለው የትህነግ ጁንታው ቡድን ለዜጎች ደህንነት ሲባል የተደረገውን የተኩስ አቁም ስምምነት በማፍረስ የአለም አቀፍ የጦር ህግና ስምምነት በተፃረረ መልኩ ዕድሜያቸው ያልደረሱ የትግራይ ህፃናትን ከፊት በማሰለፍ ለሶስተኛ ጊዜ በአማራና በአፋር ክልሎች ጦርነት በመክፈት በርካታ ንፁኃን ዜጎች ሕይወታቸውን እንዲያጡ፣ ከቤት ንብረታቸውና ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬአቸው እንዲፈናቀሉና ከፍተኛ መሠረተ ልማቶች እንዲወድሙ እያደረገ ይገኛል።
የዞናችን ህዝብ የመጀመሪያውን ወረራ ለመቀልበስ በሀብትና በገንዘብ ድጋፍና ለሠራዊቱ ስንቅ ዝግጅት በማድረግ እንደደገፈ ሁሉ አሁንም ለሶስተኛ ጊዜ በተቃጣብን ወረራ የዞኑ መንግስትና ህዝብ በገንዘብና በዓይነት ከ34 ሚሊየን ብር በላይ የሆነ ድጋፍ ለሠራዊቱ በማድረግ ደጀንነቱን እያረጋገጠ ይገኛል።
ለዚህም ለዞናችን አርሶ አደሮች፣ ለመንግስት ሠራተኞች፣ ለነጋዴዎች፣ ለባለሀብቱና ላስተባበሩ አመራሮች በራሴና በዞኑ አስተዳደር ስም ከፍ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ፤ ወደ ፊትም ጦርነቱ እስኪቀለበስ ድረስ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነቴ የጸና ነው።
ሁሉም የልማት ዕቅዶች የሚሳኩት ሠላም ሲኖር ብቻ በመሆኑ ሁላችንም የአካባቢያችንን ሠላም ለመጠበቅ ዘብ ልንቆም ይገባል።
በአገራችን ላይ የተከፈተብን ጦርነት በግንባር ውጊያ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ መስክ አንዳንድ አጋጣሚውን በመጠቀም በአቋራጭ ለመክበር በሚፈልጉ ስግብግብ ነጋዴዎች ዋጋ በመጨመርና ምርት አላግባብ በማከማቸት እንዲሁም በፕሮፓጋንዳው የማህበራዊ ሚዲያና የምዕራባውያን ሚዲያዎች በሚነዟቸው የሐሰት ወሬዎች ሳንሸበር አካባቢያችንን በትጋት ልንጠብቅ ይገባል።
የወላይታ ብሔር የብሔሩ መገለጫ የሆነው የዘመን መለወጫ "ጊፋታ" በዓልም በዚህ ወር የሚከበር በመሆኑ ድርብ ደስታ የሚሰጥ ነው።
በበዓል የተጣላ የሚታረቅበት፣ የተራራቀ የሚቀርብበት፣ ያዘነ የሚፅናናበት በመሆኑ ሁሉም የዞናችንና የሀገራችን ሕዝብ የበዓሉን ዕሴቶች ተግባራዊ እንዲያደርግ ጥሪ አቀርባለሁ።
የምናከብረው በዓል ምሉዕ ደስታ የሚሰጠን የተቸገሩትን ስንረዳ፣ የተራቡትን ስናበላ፣ የታረዙትን ስናለብስ በመሆኑ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አረጋውያንንና የተቸገሩትን ለመርዳት ያሳየነውን በጎነት በበዓላቱም አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል። በድጋሚም በዓሉ የሠላም የጤናና የብልጽግና እንዲሆን እመኛለሁ።አመሰግናለሁ!