03/04/2024
ረቡዕ መጋቢት 25/2016 ዓ፣ም ዕለታዊ ዜናዎች
1፤ የዓለማቀፉ ገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ልዑካን ቡድን ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ባደረገው ውይይት የመንግሥትን አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር መደገፍ በሚቻልበት ኹኔታ ዙሪያ ብዙ እድገት መታየቱን ገልጧል። ውይይቱ፣ ዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ዓለም ባንክ በቀጣዩ ወር መጨረሻ ገደማ በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ እንደሚቀጥል ቡድኑ ትናንት ሌሊት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የድርጅቱ ልዑካን ቡድን በአዲስ አበባ ከመጋቢት 10 እስከ መጋቢት 24 /2016 ቆይታ ማድረጉን ገልጧል። አበዳሪ አገራት የኢትዮጵያ መንግሥት እስካለፈው የፈረንጆች ወር መጨረሻ ከድርጅቱ ጋር የብድር ስምምነት ላይ ካልደረሰ፣ ለአገሪቱ እስከ ቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት ያራዘሙትን የብድር መክፈያ ጊዜ እንደሚሰርዙ እስጠንቅቀው ነበር። መንግሥት ከድርጅቱ የጠየቀው ብድር 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ነው።
2፤ ንግድ ባንክ ያላግባብ ከ121 ሺህ እስከ 95 ሺህ ብር ወስደው ያልመለሱ ደንበኞቹን ማንነት የሚገልጡ የፎቶግራፍና ሌሎች መረጃዎችን ትናንት ምሽት ለሕዝብ ይፋ አድርጓል። ባንኩ እስከ ትናንት ድረስ ያላግባብ ገንዘቡን የመለሱ ደንበኞቹ ብዛት ከ10 ሺህ በላይ መድረሱን አስታውቋል። ባንኩ ለደንበኞቹ የሰጠው የገንዘብ መመለሻ ተጨማሪ ቀነ ገደብ ዛሬ ያበቃል።
3፤ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ትናንት ምጽዋ ውስጥ የሩሲያው የባሕር ኃይል ምክትል አዛዥ አድሚራል ቭላድሚር ካሳቶኖቭ ከመሩት ልዐካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል። ውይይቱ ያተኮረው፣ የአፍሪካና ሩሲያ የመሪዎች ጉባዔ መከላከያና ጸጥታን ጨምሮ በደረሰባቸው ውሳኔዎች ዙሪያ እንደኾነ የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ የማነ ገ/መስቀል ገልጸዋል። ውይይቱ፣ ሩሲያ በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባሕር አካባቢ ለቀጠናዊ የሰላምና መረጋጋት ጥረቶች ልታደርገው በምትችለው ጥረት ዙሪያ ጭምር ያተኮረ እንደነበር የማነ ጠቅሰዋል። የሩሲያ ባሕር ኃይል ከኤርትራ ባሕር ኃይል ጋር ለዘጠኝ ቀናት ወታደራዊ ልምምድ ለማድረግ ባለፈው ሳምንት አንዲት የጦር መርከቡን ወደ ምጽዋ መላኩ ይታወሳል።
4፤ ኬንያ፣ የግል የኤሌክትሪክ ኃይል ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ ኤሌክትሪክ ኃይል ገዝተው ለአገር ውስጥ ፍጆታ እንዲሸጡ ፈቅዳለች። ኩባንያዎቹ፣ በአገር ውስጥ የተመረተ ኤሌክትሪክ ኃይልን ለሌሎች አገራት እንዲሸጡም ፍቃድ ማግኘታቸውን ቢዝነስ ዴይሊ ዘግቧል። ኬንያ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው፣ የአገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ዋጋን ለመቀነስ እንደኾነ ዘገባው አመልክቷል። ኬንያ አንድ ኪሎ ዋት ሰዓት ኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ የምትገዛው በ6.5 የአሜሪካ ሳንቲም ነው።
5፤ ኬንያ ከሱማሊያ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደማትከፍት አስታውቃለች። ኬንያ ድንበሩን የማትከፍተው፣ የአፍሪካ ኅብረት ጦር ከሱማሊያ መውጣት መቀጠሉን ተከትሎ፣ በኹሉም መውጫና መግቢያ በሮች ሊፈጠር የሚችለውን የጸጥታ ችግር በመስጋት እንደኾነ ገልጣለች። ከጥቂት ወራት በፊት ግን፣ ኬንያ ለ12 ዓመታት የዘጋችውን ድንበር ለመክፈት ወስና ነበር። ኾኖም ሱማሊያና ኬንያ የምሥራቅ አፍሪካ ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ አባል በመኾናቸው፣ በየብስ የሚደረገው የንግድ ግንኙነት ይቀጥላል ተብሏል። [ዋዜማ]