
13/06/2024
የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት | Ascension of Lord
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለስም አጠራሩ ክብር ምሳጋና ይግባውና በጌታችን በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከሚከሩ ዘጣኝ ዐበይት በዓላት መካከል የሆነው አንዱ የጌታችን ዕርገት በዓል ነው።
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በላ ከማረጉ በፊት 40 ቀን እንደቆየ ቅዱሳት መጻህፍት ይናገራሉ፡፡ " ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፥ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው።" (የሐዋርያት ሥራ 1:3) በዚህ ቃል ላይ ብዙ ነገር ተመዝግቦ እናገኛለን፡፡ 40 ቀን መቆየቱ ምክንያቶቹና ምሥጢሩ ብዙ ነው፡፡ ከነዚህም መካከል ፡-
1. የአዳም ልጅነት ስጦታ እንደተመለሰ ለማጠየቅ ፦ አዳም አባታችን በተፈጠረ በ40 ቀን ወደ ገነት በይባቤ መላእክት ገብቷል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም ዳዊት እዳለው " ወደ ላይ ዓረግህ፥ ምርኮን ማረክህ፥ ስጦታንም ለሰዎች ሰጠህ" (መዝሙረ ዳዊት 68:18) እንዳለ በምክረ ከይሲ ወድቆ የዲያብሎስ ምሮከኛ የነበረው አዳም ስጦታው (ልጅነቱ) መመለሱን ሲያረጋግጥ በ 40ኛው ቀን አርጓል፡፡
2. ዕርገቱና ትንሳኤውን እርግጥ እንደሆነ ለመናፍቃን ሊያስረግጥ ሲል፦ ክርስቶስም ይህ እንዳይሆን በሐዋ 1:2 ላይ እንደምናገኘው "በብዙ ማስረጃ ...ራሱን አሳያቸው" እንዳለ ለተጠራጣሪዎች (ዮሐ 20:24-29) ሕማሙ ሞቱ ትንሳኤው እርግጥ ፤ እውነት እነደሆነ ለማስረገጥ 40 ቀን ቆይቷል፡፡
3. የሐዋርያትን ሃይማኖት ለማጽናት፦ ተስዕሎተ መልክ (የሰው ልጅ ተፀንሶ በማህፀን ሳለ ሙሉ የሰው ቅርጽ እስከሚይዝ ድረስ ያለው ጊዜ) በ40 ቀን እንየሚፈጸም ክርስቶስም በጽንስ ያለውን የሐዋርያትን እምነት ለማጽናት ሲል 40ቀን ቆይቷል፡፡ "ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፥" (የሐዋርያት ሥራ 1:3) ክርስቶስ በ 40 ቀን ቆይታው ብዙ ትምህሮቶችን አስተምሯቸዋል፡፡ ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት በተለይም መጽሐፈ ኪዳንን አስተምሯል፡፡
ክርስቶስ ያረገው በደብረዘይት ጥግ በምትገኘው በቢታንያ ነው፡፡ ሉቃ 24:50 ቢታንያ ከኢየሩሳሌም 15 ምዕራፍ ትርቃለች፡፡ ቢታንያ አልአዛርን ከሞት ያስነሳበት ፤ መግደላዊት ማርያም ሽቱ በእግሩ አፍሰሳ ንስሐዋን የተቀበለበት እንዲሁም ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ ሆነ ሲመጣ ያርፍባት የነበረች ከተማ ናት፡፡ እርሷም ምትገኘው ከኢየሩሳሌም በስተ ምስራቅ ነው፡፡ በዚህ እደሚያርግ ነብዪ ዳዊት እንዲህ ብሎ ተንብዮ ነበር፡፡ " በምሥራቅ በኩል ወደ ሰማየ ሰማያት ለወጣ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ የኃይል ቃል የሆነ ቃሉን፥ እነሆ፥ ይሰጣል።" (መዝሙረ ዳዊት 68:33)
ሊቃውንተ ቤ/ን የጌታችንን ዕርገት ወቅቱን ከልደቱ ጋር አገናኝተው ደስ በሚያሰኝ ሚስጢር ይተረጉሙታለ፡፡ በተለይ ስለ ጠፈር ምርምር ትልቅ ዕውቀት እንዳለው የሚነገርለት አባታችን ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ እንዲህ በማለት ያብራራል "ጌተችን የተወለደው በወርኃ ታኅሳስ ነው በዚህ ወቅትም ፀሐይ ከምህዋራ ዝቅ የምትልበት ጊዜ ነው፡፡ እውነተኛው ፀሐይ ክርስቶስም በፍጹም ፍቅሩ ዝቅ ብሎ በዚህች ወር ተወለደ፡፡ እንዲሁም በወርኃ ግንቦቶ ፀሐይ ከምህዋሯ ከፍ የምትልበት ከሌላው ጊዜ በበለጠ የምታሸበርቅበት የምታበራበት ወቅት ነው፡፡ እውነተኛው ፀሐይ ክርስቶስም ከምድር ከፍ ብሎ በርቀት ሳይሆን በርህቀት ዐረገ፡፡"
ከበዓሉ ረድኤት በረከት ያሳትፈን ....
አሜን!!
Natnael Yaboneh