![የከተራና ጥምቀት በዓል በዞኑ ሁሉም አካባቢዎች ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የሀድያ ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ። ህብረተሰቡም ...](https://img4.medioq.com/028/359/1052221910283594.jpg)
17/01/2025
የከተራና ጥምቀት በዓል በዞኑ ሁሉም አካባቢዎች ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የሀድያ ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።
ህብረተሰቡም በዓሉን ሲያከብርም የራሱን እና የአከባቢውን ሰላም በማስጠበቅ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመሆን የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ጥሪውን አስተላልፏል።
።።።።።።።።።ሆሳዕና፣ ጥር 9/2017 ዓ.ም።።።።።።።
የሀድያ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ተሾመ ባቲሶ የጥምቀት በዓል በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
አዛዡ በሰጡት መግለጫ እንደገለፁት በአለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገበዉ የከተራና የጥምቀት በዓል ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ ኃይማኖታዊ ትውፊቱ ተጠብቆ ባማረና በደመቀ ሁኔታ በዞኑ ሁሉም አካባቢዎች እንደሚከበር አስታውሰው።
በዓሉ በዘንድሮ ዓመትም በዞኑ በሁሉም አካባቢዎች በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተደርጎ አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል።
የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ተሾመ ባቲሶ አያይዘውም እንዳብራሩት ታቦታቱ ካሉበት ወደ ጥምቀተ ባህሩ ከሚወርዱበት ከከተራ ዕለት ጀምሮ ተገቢውን እጀባ ከማድረግ ባለፈም በማደሪያቸው ተገቢው ጥበቃ ተደርጎ ወደ ደብራቸው እስኪመለሱ ድረስ ፖሊስ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ተገቢውን ጥበቃ ማድረግ እንዲቻል በዞኑ በሚገኙ ሁሉም የፖሊስ መዋቅሮች አባላት መመደባቸውንም ተናግረዋል።
ዋና አዛዡ አያይዘውም በዓሉ በሰላም እንዲከበር የፀጥታ ኃይሉ፣ የፓትሮል ቅኝት ከማድረግ ባለፈም የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም በዕለቱ ሊፈጸሙ የሚችሉ ወንጀሎችን ለመከላከል የፀጥታ ኃይሉ ዝግጅቱን አጠናቆ በስምሪት ላይ ይገኛል ብለው፤
ህብረተሰቡም በዓሉን ሲያከብር የራሱን እና የአከባቢውን ሰላም በማስጠበቅ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመሆን የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል በማሳሰብ ጥሪ አቅርበዋል።
በመጨረሻም የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ተሾመ ባቲሶ ለመላዉ የእምነቱ ተከታዮች ለ 2017 ዓ.ም እንኳን ለከተራ እና ለጥምቀት በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል ።