22/10/2024
በሐረሪ ክልል የመኸር እርሻ እስከ አሁን 11 ሺህ 774 ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል - የክልሉ ግብርና ቢሮ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2017(ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል የመኸር እርሻ ወቅት እስከ አሁን 11 ሺህ 774 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ልማት ቢሮ ኃላፊ ሮዛ ኡመር እንደገለፁት፦በክልሉ በተለይም በአሁኑ ወቅት ፆም ሲያድር የቆየ መሬት ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ ጭምር ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጂነት ለመላቀቅ በቁርጠኝነት እየተሰራ ይገኛል።
ለዚህም የማዳበሪያ፣የዘርና ሌሎች የግብርና ግብዓት አቅርቦት በማሟላት የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት የማሳደግ ስራ በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉን ተናግረዋል።
በየደረጃው ያሉ የግብርና ባለሙያዎችም ለአርሶ አደሩ አስፈላጊውን ሙያዊ እገዛና ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም አርሶ አደሩን ከዝናብ ጠባቂነት ከማላቀቅና ተጠቃሚነትን ከማሳደግ አንፃር አበረታች ስራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት።
በክልሉ በተለይም ለስንዴ፣ ለማሽላ ፣ ለአትክልትና ፍራፍሬ ልዩ ትኩረት በመስጠት በክላስተር እየለማ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
አርሶ አደሩ እያከናወናቸው ያሉ የተቀናጀ የግብርና ልማት ስራዎች ምርታማነትን በማሳደግ የከተማውን ሕዝብ የኑሮ ውድነት ጫና ለመቀነስ ፋይዳው የላቀ መሆኑን አመልክተዋል።
በክልሉ የመኸር እርሻ እስከ አሁን 11 ሺህ 774 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ጠቅሰው፦ በማሳያነትም 450 ሄክታር መሬት በስንዴ እንዲሁም 800 ሄክታር መሬት በአጭር ጊዜ ምርት በሚሰጥ የማሽላ ኢንሼቲቭ መሸፈኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም የተገኙ አበረታች ውጤቶችን በማስቀጠል የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማጎልበትና ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የላቀ ትኩረት እንደሚሰጥ መናገራቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።