11/01/2025
በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ መግለጫ
የከምባታ ዞን አስተዳደር በአዲሱ የመዋቅር አደረጃጀት በአዲስ መልክ ዞን ሆኖ ከተዋቀረ ማግስት ጀምሮ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በመሠረተ ልማት ዘርፈ ብዙ የልማት ተግባራትን እያከናወነ መቆያቱ ይታወቃል።
ዞኑ እስካሁን ባለው ሁኔታ የሀሳብ ልዕልናን በማስቀደም በየጊዜው የሚያጋጥሙ ያለመግባባት ችግሮችን በምክክር እና በውይይት በመፍታት ተግባራዊ ሲያደርግም ቆይቷል።
በአሁን ወቅት ለህዝባችን ከመተባበር ይልቅ መገፋፋትን ፤ ከመደጋገፍ ይልቅ መጠላለፍን፤ ከሰላማዊ ውይይትና ድርድር ይልቅ መጠፋፋትን እንደ አማራጭ አድርጎ የያዙ አካላት ከዚህ አይነት ለህዝባችን ምንም ከማይፈይድ እንቅስቃሴ ፈጥነው በመላቀቅ ከብልጽግናው መንግስታችንና ከህዝባችን ጎን በመቆም በዞናችን ከጫፍ ጫፍ የተጀማመሩ የልማት አጀንዳዎችን በማንቀሳቀስ አሻራቸውን እንዲያስቀምጡ እያሳሰብን ከመወቃቀስና ከመጠላለፍ አጀንዳዎች ወጥተን በቀና ልብ ለህዝባችን የሚበጁ ሀሳቦችን ማንሸራሸር ላይ ማተኮርን መለማመድ ይኖርብናል።
ለህዝባችን የሚያስፈልገው ልማት፣ ሰላም፣ ፍቅር፣ ወንድማማችነት፣ እህትማማችነት፣ አንድነት፣ ዴሞክራሲን መጎልበት፣ መልካም አስተዳደርን መረጋገጥና ብልፅግና ናቸው ያለው መግለጫው ለዚህ ስኬት ደግሞ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን በግንባር ቀደምትነት መወጣት ይገባል በማለትም አሳስቧል።
ሰሞኑን በተለያዩ የማኅበራዊ ድረ -ገጾች ከእውነታው ጋር ፈጽሞ የማይገናኙ በአሉባልታና በሐሰት መረጃዎች መነሻ የሚናፈሱ ወሬዎች ልማታዊና ሰላማዊ የሆነውን የከምባታንና የዶንጋን ማኅበረሰብ ሆን ተብሎ በተፈበረከ ወሬ ለማደናገር እየተሞከረ መሆኑን እያስተዋልን ነው ያለው መግለጫው አንዳንድ የማኅበራዊ ድረ-ገጽ ባለቤቶች እንዲሁም ሌሎች ፌክ አካውንት ከፍተው ብዥታ የሚነዙ ግለሰቦችና ቡድኖች ከዚህ ዓይነቱ ሕገ-ወጥ ተግባራቸው ሊቆጠቡ ይገባል በማለት በመግለጫው ጠቅሷል።
በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የዞናችን ተወላጆችና የልማቱ ደጋፊዎች ሀገር ቤት ለሚካሄደው ልማት በራሳቸው ተነሳሽነት በከፍተኛ ንቅናቄ ሰብስበው ያስረከቡትን ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ ሳይውል ተበልቷል በሚል አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ እየተሠራበት ይገኛል።
በተሰበሰበው ገንዘብ ለመሠረተ ልማት ሥራ የሚያገለግሉ ማሽነሪዎችን ለመግዛት የክልል ፋይናንስ ቢሮ ሲኒየር ባለሙያዎችን ጨምሮ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተወጣጣ የቴክኒክ ቲም ተቋቁሞ ሕጋዊ የጨረታ ሂደቱ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል።
ለዚሁ ዓላማ 22,050,925.36 (ከሃያ ሁለት ሚሊዮን) ብር በላይ የተሰበሰበውን ሀብት ጨምሮ ከሌሎችም ምንጮች በማስተባበር የታሰበውን የማሽነሪ ሙሉ ክሩ ለመግዛት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ባለበት በዚህ ወቅት ፀረ-ልማት ኃይሎች በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ ለእኩይ ፖለቲካዊ ግባቸው በተናበበ መልኩ የሚያካሂዱት ዘመቻ ከአፍራሽነቱ ባሻገር ለሕዝቡ የሚፈይደው ነገር አይኖርም ብሏል መግለጫው
በሌላም በኩል ባሳለፍነው በጀት ዓመት የዞናችን ባለ ብሩኅ አዕምሮ ተማሪዎች በሒጋ ሞዴል አዳሪ ትምህርት ቤት ሲማሩ በበጀት እጥረት ምክንያት ችግር ተፈጥሮ በዞኑ አስተዳደር በኩል ለወገን የድጋፍ ጥሪ ቀርቦ በተደረገው ርብርብ (4,484,544) አራት ሚሊዮን አራት መቶ ሰማኒያ አራት ሺህ አምስት መቶ አርባ አራት ብር) ድጋፍ ተገኝቶ አመርቂ ውጤት ከመመዝገቡም በላይ የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች በሙሉ (147 ተማሪዎች) ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ገብተዋል።
ይህ አይነት ከዚህ ቀደም ያልተለመዱ ግን ደግሞ ህዝባችንን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በጎ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ተገልጿል።
በዚሁ መሠረት ዞናችን በተያዘው 2017 በጀት ዓመት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የአከባቢውን ተወላጆችና የልማት ወዳድ አካላትን በማቀናጀት ሀብት የማሰባሰቡ ተግባር ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ከሀገር ውስጥ የአከባቢውን ባለሀብት ነጋዴዎችንና ተቋማትን ከዞኑ አስተዳደር ጋር በቅንጅት በማወያየት ከ56 ሚሊዮን ብር በላይ ቃል የተገባ ሲሆን የከምባታ ዞን መሠረተ ልማት ሥራዎች ሀብት ማሰባሰቢያ በተከፈተው ልዩ አካውንት ገቢ የማድረግ ሥራ ተጀምሯል።
በተለይ በአሁኑ ወቅት ለመሠረተ ልማት ሥራ በዞናችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከደቡብ አፍሪካ ተወላጆችና ከልማት ወደጆች በተገኘው ፈንድ ማሽናሪ ግዥ ለማከናወን ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ ባሉበት ሁኔታ የተጀመረውን የልማት እንቅስቃሴ ጠል በሆኑ ግለሰቦች በጭፍን አመለካከት በተወሰዱ መረጃዎች መነሻ የተነሣው ጉዳይ ፈጽሞ የተሳሳተና የተቋሙን የሥራ ሞራል የሚጎዳ እንዲሁም የተጀመረውን የደቡብ አፍሪካ ሀብት አሰባሰብን በሚያጨልም ሁኔታ የተገለጸበት የተዛባ አመለካከት ፈጥኖ መታረም እንዳለበትና ለሕዝቡ ትክክለኛውን ሥዕል ማስያዝ እንደሚጠበቅባቸው በመግለጫው ተጠቅሷል።
በመጨረሻም በሐሰት መረጃ ተንተርሶ ከዞን እስከ ክልል ከፍተኛ አመራሮቻችን ዙሪያ የተገለጸው መልዕክት ፍጹም የተሳሰተና ከእውነታው የራቀ መሆኑ ታውቆ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ሀገራት ያላችሁ የልማት ወዳዶች የተጀመረውን የሀብት አሰባሰብ የልማት ንቅናቄ በተቀናጀና በተባበረ ክንድ እውን ለማድረግ መረባረብ ቀዳሚው ተግባር መሆን እንዳለበት መግለጫው አስታውቋል።
የከምባታ ዞን መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ