
25/01/2025
በኢንቨስትመንት ዘርፉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት እየሠራ መኾኑን የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ገለጸ።
አዲስ አበባ: ጥር 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር አዲስ አበባ ከሚኖሩ የደብረ ብርሃን ከተማ ተወላጅ ባለሀብቶች ጋር በሰላም እና በልማት ዙሪያ መክሯል።
የባለሀብቱ የገቢ ምንጭ መዳከም፣ የፋይናስ ተቋማት የብድር አቅርቦት ችግር መኖር በከተማዋ በሚፈለገው ልክ ኢንቨስት ለማድረግ ፈታኝ መኾኑን ባለሀብቶቹ አንስተዋል።
በተለይም ደግሞ በአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ቀልጣፋ እና ፍትሐዊ አገልግሎት አለመኖር፣ ከተማውን እና ወረዳውን የሚያስተሳስር የመንገድ መሠረተ ልማት አለመሟላት ለልማት እንቅፋት መኾናቸውን ነው የጠቆሙት።
እነዚህ ችግሮች በመንግሥት በኩል እንዲፈቱ እና አስፈላጊው ትብብር እንዲደረግላቸውም ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በከተማ አሥተዳደሩ የአምራች ኢንድስትሪውን የልማት እንቅስቃሴ የሚያስቆም ምንም አይነት የጸጥታ ሥጋት እንደሌለ አንስተዋል።
በከተማው ያለውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም ለማሸጋገር ኅብረተሰቡ እና መሪዎች በቁርጠኝነት እየሠሩ መኾኑንም ጠቁመዋል።
ከተማዋን ለማልማት የባለሀብቶች ሚና ከፍተኛ መኾኑን የጠቀሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ኢንቨስት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
ባለሀብቶች ኢንቨስት ማድረግ የሚችሉበት አስቻይ ኹኔታዎች በከተማ አሥተዳደሩ በኩል ማዘጋጀታቸውን ነው የተናገሩት። በከተማዋ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች በታለመላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ እና መሬት ወስደው ወደ ልማት ያልገቡ ባለሀብቶች እንዲያለሙም አሳስበዋል።
ለኢንዱስትሪ ዘርፉ አጋዥ የኾኑ እንደ መንገድ፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ እና ሌሎች የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች እየተገነቡ ነው ብለዋል።
ከአሁን በፊት በከተማው የነበረው ትልቁ ችግር የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ነበር ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አሁን ላይ ችግሩን የሚፈታ ሥርዓት ተዘርግቶ እየተሠራ ነው ብለዋል።
አልሚ ባለሀብቶች ከመሬት ጋር የሚያነሱትን የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታትም ከተማ አሥተዳደሩ ከምንጊዜውም በበለጠ በቁርጠኝነት እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። የብድር አቅርቦት ችግሩ እንዲፈታ ከፋይናንስ ተቋማት ጋር ምቹ ሁኔታ ለመፍጠርም በጋራ እንሠራለን ነው ያሉት።
የከተማውን ዕድገት የሚመጥን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን በሁሉም አገልግሎት ሰጭ ተቋማት የዲጅታላይዜሽን አገልግሎት ተግባራዊ እየተደረገ ስለመኾኑም አብራርተዋል።
ዘጋቢ:- ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation