08/11/2025
የአብሬት ሼህ መስጂድ ታሪካዊ ቅርስነቱ በጠበቀ መልኩ የማስፋፊያ ግንባታ ሊደረግለት መሆኑን ተገለፀ!!
ጥቅምት 29/ 2018 ዓ ም(ወልቂጤ)
በጉራጌ ዞን ከሚገኙ ታሪካዊና ጥንታዊ ስፍራዎች ውስጥ አንዱ የሆነው የአብሬት ሼህ መስጂድ በአዲስና ዘመናዊ ዲዛይን ከ200 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የማስፋፊያ ግንባታ ሥራ በይፋ ተጀምሯል።
የፕሮጀክቱ ማስፋፊያ ግንባታ የመስጂዱን ታሪካዊ ቅርስነት በመጠበቅ፣ ዘመኑ የሚጠይቀውን የመማርያና የአምልኮ አገልግሎት ባካተተ መልኩ ለመገንባት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
ከዛሬ 147 ዓመት በፊት በዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ ዘመነ መንግስት እንደተመሠረተ የሚነገርለት መስጂዱ የእምነት ቦታው እንደ ጥንታውያን ጋሻዎች፣ ሰይፎች፣ ጦሮች፣ የቁርኣን ጥቅልሎች፣ መጽሐፎች እና የትርጉም ሥራዎች፣ የእንጨት ልባሶች፣የጠፈር አልጋዎች እና የማስተማሪያ መሳሪያዎች የመሳሰሉ ብርቅዬ ቅርሶችን በውስጡ ይዟል።
አዲሱ የሚሰራው መስጂድ ሁሉንም ነገር ያካተተ ሲሆን፣ ሂፍዝ ማዕከል(የቁርኣን መሐፈዢያ) ጨምሮ የተሟላ የአምልኮ እና የማስተማሪያ ተቋም እንደሚኖረውም ተገልጿል።
የአብሬት ሼህ ልጅ የሆኑት ሰይድ ፋቲህ ሰይድ እንደተናገሩት የግንባታው ዋና ዓላማ፣የመስጂዱን ታሪካዊነት በማስቀጠል የቅድመ አባቶች ራዕይን እውን ማድረግ መሆኑንና ለቀጣይ ትውልድ የሚተላለፍ ትልቅ ሀብት ለማኖር መሆኑን ገልጸዋል።
አብሬት ሼህ መስጂድ የጉራጌ ዞን ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ የታሪክ አካል ነው ያሉት ሰይድ ፋቲህ ይህንን መስጂድ በአዲስ መልክ የመገንባቱ ሥራ፣ ለሃይማኖታዊ ትውፊቶቻችንና ቅርስ አክብሮት እንዳለን ያሳያል ብለዋል።
በፕሮግራሙ የተገኙት ዶክተር መሐመድ ጀማል በበኩላቸው እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ የሀይማኖትና የቅርስ ጥበቃ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ገልጸው ይህ ታላቅ ፕሮጀክት የመስጂዱን ታሪካዊ እሴት ከመጠበቁም በላይ፣ በአካባቢው ለሚገኙት ወጣቶች ዘመናዊ የሃይማኖት ትምህርት ለመስጠት ያለመ ነው ብለዋል።
መስጂዱ የሁሉም ነገር ማዕከል (ሂፍዝ ማዕከልና ቁርኣን መቅሪያ) በመሆን የወረዳችንን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ሚና ያሳድጋል ብለዋል።
የቸሃ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሱ ድንቁ እንደተናገሩት ታሪካዊ ቦታዎችን ማልማትና መጠበቅ የባህልና የልማት አካል መሆኑን አብራርተዋል።
የአብሬት መስጂድ የማኅበረሰባችንን ታሪክና መንፈሳዊ ትስስር የሚወክል ትልቅ ሀብት ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ይህ ታላቅ የማስፋፊያ ግንባታ ፕሮጀክት የሃይማኖት ተቋማት በወረዳችን ልማት ማኅበራዊ ትስስርና የቱሪዝም ፍሰት ላይ ያላቸውን ጠቀሜታ ያሳድገዋል ብለዋል ።
የፕሮጀክቱ ስኬት የእምነት ቦታውን ዘመናዊነት በማረጋገጥ፣ ለዘመናት የቆየውን የሃይማኖት መቻቻል ታሪክን የሚያጠናክር ይሆናል ብለዋል!!
በግንባታው ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ የቸሃ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሱ ድንቁ ጨምሮ የአብሬት ሼህ ልጆች ፣የወረዳው ከፍተኛ አመራሮችና ሌሎችም ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል ሲል የዘገበው የቸሀ ወረዳ መ/ ኮ ፅ/ቤት ነው!!