20/10/2021
በጣም ካደነቅኳቸው መጻሕፍት አንዱ
---------
አፈንዲ ሙተቂ
-------
በአማርኛ ቋንቋ የነቢዩ ሙሐመድን (ሰዐወ) የህይወት ታሪክ የሚተርክ መጽሐፍ በማዘጋጀት ከሁሉም የሚቀድሙት ሐጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብ ሲሆኑ ዘመኑ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1961 ነው። በተመሳሳይ ርእስ የተጻፈው ሁለተኛ መጽሐፍ ደግሞ የፊት ሽፋኑ በዚህ ፎቶ ላይ የተመለከተው ነው። የመጽሐፉ ደራሲ ወልደገብርኤል አሰጌ ይባላሉ። መጽሐፉ የታተመበት ዘመን 1965 ነው።
በዚህ መጽሐፍ ከተጻፈው ታሪክ በላይ በብዙዎች ዘንድ የተደነቀው የደራሲው ነፃ እና ሚዛናዊ የሆነ አቀራረብ ነው። አውሮጳዊያንና አሜሪካዊያን እንኳ የነቢዩን ታሪክ በትክክለኛው መልኩ ለመጻፍ አዕምሮአቸው በሚለግምበት ዘመን በሀገራችን ውስጥ እንዲህ ዓይነት ሚዛናዊ ድርሰት ተጽፎ ነበር።
ደራሲው መጽሐፉን ከማሳተማቸው በፊት ረቂቁን ለሁለት ታላላቅ ዑለማዎቻችን አሳይተው ነበር። እነዚያ ዑለማ ሐጂ ዩሱፍ ዐብዱራሕማን ገራድ እና ሐጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብ ናቸው። ሁለቱ ዑለማ ረቂቁን ካነበቡ በኋላ በደራሲው ሚዛናዊነት ተገርመው በጻፉት መቅድም ውስጥ የሚከተለውን ምስክርነት ሰጥተዋል።
"መጽሐፉን ከተመለከትን በኋላ እንደተረዳነው ደራሲው ምንም እንኳ በግል እምነታቸው ክርስቲያን ቢሆኑም የታሪክን ትክክለኛ ዓላማ ተከትለው አድልዎ በሌለበት ቅን መንፈስ ተመርተው እውነተኛውን ተግባር በመመራመርና የህሊናቸውን እውነተኛ ፍርድ በመስጠት ባደረጉት ሙከራና ባሳዩት አርቆ አስተዋይነት ለሀገራቸው አንድነት ቅን አስተሳሰባቸውን ከማረጋገጣቸውም በላይ በሁለቱ ሀይማኖቶች በሚያምኑ ኢትዮጵያዊያን መካከል የመቀራረብንና የመግባባትን መንፈስ የሚያፋፋ አንድነትን ለማጠንከር የሚረዳ መሆኑን ለመረዳት ቻልን"
ሐጂ ዩሱፍ ዐብዱራሕማን (የደጃች ዑመር ሰመተር ት/ቤት ዲሬክተር)
ሓጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብ (የመስጊድ አል-አንወር አሰጋጅ)
----
ይህንን መጽሐፍ በቅድሚያ ያነበብኩት በልጅነቴ (በ1980 ገደማ) ነው። ሁለቱ ዑለማ በአጽንኦት የጠቀሱትን የደራሲውን ሚዛናዊነት በደንብ ተረድቼ ለመጽሐፉ አድናቆቴን የሰጠሁት ግን በ1990 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለሁ በድጋሚ ባነበብኩበት ወቅት ነው። በርግጥም መጽሐፉ በገጽ ብዛቱ አነስተኛ ቢሆንም ታሪክን መጻፍ የሚፈልግ ሁሉ እንደ ሞዴል ሊገለገልበት የሚገባ ድርሰት ነው።
-------
አፈንዲ ሙተቂ
ጥቅምት 8/2014