
08/11/2017
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሾመ
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የዳይሬክተሮች ቦርድ አቶ ወንድምአገኘሁ ነገራን የገበያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አድርጎ ሾመ።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አቶ ወንድምአገኘሁ ነገራ የምርት ገበያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ከመሾማቸው በፊት የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ካቢኔ አባልና የንግድና ግብይት ልማት ቢሮ ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ ነበሩ።
ቀደም ሲልም የኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ ፕሬዚዳንት እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዝዲንት ሆነው አገልግለዋል።
አቶ ወንድምአገኘሁ ነገራ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በአካውንቲንግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያገኙ ሲሆን፥ በቢዝነስ አመራር ከደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ እና ከአሜሪካ በማኅበራዊ ሳይንስ የማስተርስ ድግሪዎችን አግኝተዋል።
የሥራ አመራር ቦርዱ ከዋና ሥራ አስፈጻሚ ሹመት በተጨማሪ ሁለት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚዎችን ሾሟል።
በዚህ መሰረት አቶ በላይ ጎርፉ የግብይትና ገበያ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና አቶ መርጊያ ባይሳ የመጋዘንና የጥራት ኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ተሹመዋል።
አቶ ወንድምአገኘሁ የምርት ገበያው አራተኛ ዋና ስራ አስፈፃሚ ናቸው።
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ)