16/04/2024
የሸዋል ኢድ
ትንሹ ኢድ ተብሎ ስለሚጠራው፣ የረመዳን ወርና የረመዳን ጾምን ማብቃት ተከትሎ ዐስረኛ ወር በሆነው ሸዋል ስለሚመጣው፣ በሐረሪ ሰዎች ደግሞ በድምቀት ስለሚከበረው ስለ ሸዋል ኢድ ልናወሳ ነው። ከዛ ቀድመን ግን በዓሉ ከሁሉ መርጦ ስለከተመባት ሐረር ጥቂት እንበል።
ከአዲስ አበባ 525 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ሐረር፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ የሥልጣኔ ማሳያ እንደሆነች ይነገርላታል። ለዘመናትም ከፍተኛ የንግድ ማዕከል ሆና አገልግላለች። በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ለጥበቃዋ ተብሎ የተሠራው የጀጎል ግንብ ዛሬ ቅርስና ውበቷ ሆኖ ይገኛል። አልፎም ይኸው የጀጎል ግንብ እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2006 በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም የዓለም ቅርስ ተብሎ ተመዝግቦላታል። ባለ አምስት በሩ የጀጎል ግንብ፣ የሐረር ከተማ በአነስተኛ የመሬት ስፋት በርካታ ጎብኚዎችን ከሚያስተናግዱ ጥቂት የዓለማችን ከተሞች አንዷ እንድትሆን አድርጓታል።
እንግዲህ ሸዋል ኢድ በድምቀት የሚከበረው በዚህች አንጋፋ፣ ጥንታዊትና ውብ ከተማ ነው። በዓሉ በሐረሪ ክልላዊ ሕዝባዊ እና ባህላዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር በአዋጅ የተደነገገው ጥቅምት 8/1999 ዓ.ም ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮና በኋላም ባህላዊ እሴቱ እየጎላና እየበረታ ሄዶ፣ ከሐረር አልፎ ለኢትዮጵያ፣ ከኢትዮጵያ ተሻግሮም የዓለም ቅርስ ለመሆን በቅቷል። የበዓል አከባበሩን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ በ2012 የተጀመረው ሥራና ጥረት ፍሬ አፍርቶ፣ ባሳለፍነው ዓመት የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የበዓሉን አከባበር ከዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል ጽፎታል።
በመግቢያችን እንዳነሳነው ሸዋል ኢድን አንዳንዶች ‘ትንሹ ኢድ’ ብለው ይጠሩታል። ምክንያቱ ደግሞ የጾሙ ቀናት ጥቂት መሆናቸው ነው፤ ስድስት። ‘ሸዋል’ የሚለው ዋና መጠሪያው ደግሞ የረመዳን ወር ማብቂያና የኢድ አልፈጥርን በዓል ተከትሎ የሚመጣውን ዐስረኛ ወር ሸዋልን መሠረት ያደረገ ነው።
የሸዋል ኢድ ባህላዊ ትርክትና ሥርዓቱ እንደሚያመዝን የሃይማኖቱ አዋቂዎች ይናገራሉ። ሃይማኖታዊ መሠረቱን በሚመለከት የሚያስረዱ ሰዎችም ሲናገሩ “ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የረመዳን 30 ቀን ጾም ሲያበቃ 6 ቀን ሸዋልን የጾመ ዓመቱን ሙሉ እንደጾመ ይቆጠርለታል ብለዋል።” ይላሉ። ይህንንም እንዲህ ሲሉ ያብራሩታል፥ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ሰው መልካም ሥራ ሲሠራ፣ በአላህ ዘንድ ዐስር እጥፍ ይሆናል ተብሎ ይታመናል። ስለዚህ በዓመት 360 ቀናት አሉና፣ 30 ቀናት የረመዳን ጾም እንደ 300 ቀን፣ 6 ቀኑ ደግሞ እንደ 60 ይታሰባል። ‘ዓመቱን ሙሉ እንደጾመ ይቆጠርለታል’ የሚባለው ከዚህ የተነሳ ነው።
አበው ነገርን አንድም እያሉ በአንድምታ እንደሚያስረዱ፣ የሸዋል ኢድ አንድም ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት መነሻነት የሚታሰብ ሲሆን፣ አንድም ነገረ ሴቶችን ያጣቅሳል። ይህም በእስልምና አስተምህሮ ሴቶች በረመዳን ጾም ወቅት የወር አበባ በሚያዩባቸው ቀናት ጾሙን ያቋርጣሉ። በዚህም የተነሳ ያጎድሉትን የጾም ቀናት ለማካካስ እንዲችሉ ለማድረግ የረመዳንን መጠናቀቅ ተከትሎ የሚመጡ ቀናትን በጾም ያሳልፋሉ። ወንዶችም ታድያ ተጨማሪ ትሩፋት ለማግኘት ጾሙን አብረው ይጾማሉ።
እናም እነዚህን መሠረት አድርጎ ሕዝበ ሙስሊሙ ሸዋልን ይጾማል። ከረመዳን ወር ጾም ባገኘው የመንፈስ ጥንካሬ ቀጥሎ፣ በኢድ ማግስት ሸዋልን ይጀምራል። ታድያ የስድስት ቀኗን ጾም ተከትሎ፣ የበዓል አከባበር ሥርዓቱ በጋራ መሰባሰብ፣ ስጦታ መሰጣጠትን የመሰለ ክዋኔን ያካትታል። እንደ ሃይማኖቱ መምህራን ገለጻ፣ እነዚህና እነዚህን የመሰሉ በዓሉን የተከተሉ ክዋኔዎች በባህል ተለምዶ የሚካሄዱ መሆናቸውን ሲያስረዱ፣ በሃይማኖት ‘እንዲህ ስለተባለ...’ ተብሎ የሚጠቀስ መደገፊያ እንደሌለው ይገልጻሉ።
ሸዋል ኢድ በአዋጅ ተደንግጎ በድምቀት በአደባባይ የሚከበርባት ሐረር፣ በዚህ ወቅት ከውጭም ከውስጥም በርካታ እንግዶችንና ጎብኚዎችን ታስተናግዳለች። ‘የሐረሪ ባህላዊ ኢድ’ ተብሎ እንዲጠራም ያደረገው ይህ ድምቀቱ ነው። ታድያ በበዓሉ ከሚታዩ ክዋኔዎች አንዱ በዝክሪ ለፈጣሪ ምስጋና በማድረስ ሲሆን፣ ዝክሪ በምስጋና ግጥሞች የተመላ ነው።
ልጃገረዶችም ታድያ በዓሉን ተከትሎ በሚኖሩ ሦስት ተከታታይ ቀናት ከሥራ ነፃ ሆነው የገንዘብ መዋጮ (መሐለቅ መታጫ) በማድረግ ድግስ አዘጋጅተው በመመገብና በመጨፈር በዓሉን ያከብራሉ። ከዝክሪውና ከዚህ የሴቶች የጎላ ሱታፌ በተጨማሪም፣ ባህላዊ ምግብ እና መጠጥም የበዓሉ አካል ነው። የበዓሉን መድረስ ተከትሎ የሚነሱና በበዓሉ ሰሞን ከሚዘወተሩ ምግቦች መካከል አቅሌል፣ ሐሸር ቃሕዋ፣ ቁጢ ቃሕዋ ይጠቀሳሉ። (አቅሌል፣ በቀይ ወጥ የተዘጋጀ ፍትፍት ሲሆን፣ ሐሸር ቃሕዋ እና ቁጢ ቃሕዋ ከወተት ጋር ተፈልቶ የሚጠጣ ቡና እና ሻይ ነው።)
በዚህ ሰሞን በየትኛው ቦታ ያለ ሰው ወደ ሐረር አቅንቶ ከቤተሰቡ ጋር ይዘያየራል፣ ያላገቡ ይተጫጩበታል። ሕዝብ በከፍተኛ ቁጥርና ማራኪ ባህላዊ ቀለም አልባሳት ይደምቃል።
ሸዋል ኢድ በሐረር በዚህ መጠን ይድመቅ እንጂ፣ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎችም ይከበራል። እንደውም እንደየ አካባቢው ክዋኔውም ይለያል። ለምሳሌ ሸዋል ኢድ በስልጤዎች ዘንድ ትዳር የያዙ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ቤተሰቦቻቸውን የሚጠይቁበት ቀን ነው። በወለኔዎች ደግሞ የኢድ ማግስት ጾም ስለሆነ ኢድ አልፈጥርን ብዙ አይዘጋጁበትምና ከስድስቱ ቀናት ጾም ፍቺ በኋላ የሚመጣውን የሸዋል ኢድ ሰፊ ዝግጅት አድርገው ያከብሩታል።
አምባሰል ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን