11/11/2023
የተመዘገቡ ውጤቶችን በማጠናከር ተግዳሮቶችን ለማለፍ አመራሩን በዕውቀትና በክህሎት የመገንባት ተግባር እየተከናወነ ነዉ:-አቶ ፀጋዬ ማሞ
የተመዘገቡ ውጤቶችን ለማጠናከርና የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በማለፍ ብልፅግናን ለማረጋገጥ አመራሩን በእውቀትና በክህሎት ማብቃት ትኩረት የተሰጠው መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ ገለፁ።
"ከዕዳ ወደ ምንዳ'' በሚል መሪ ቃል 3ኛ ዙር የመንግስት አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና መድረክ በቦንጋ የስልጠና ማዕከል ትናንት ተጀምሯል።
በመክፈቻው ላይ የክልሉ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ እንደገለጹት፤ እንደ ሀገር እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶችን ለማጠናከርና መልካቸውን እየቀያየሩ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ለመሻገር አቅምን መሰብሰብና አመራሩን ማብቃት ያስፈልጋል።
በተለይም የፊት አመራሩ ወቅቱ የሚጠይቀውን የአመራር ክህሎትና ብቃት በማዳበር ድሎችን በማጠናከርና ዕድሎችን በተሳለጠ መንገድ ወደ ውጤት መቀየር ይጠበቃል ብለዋል።
ከዚህ ባሻገር ፈተናዎችን በብልሃት በመሻገር የዕድገት ግቦችን የሚያሳኩ እንዲሆኑ አመራሩን የማብቃት ስራ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።
የብልፅግና ፓርቲ መንግስት ሆኖ ሀገርቱን መምራት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ያስመዘገባቸው በርካታ ውጤቶች መኖራቸውን ገልጸው በሂደቱም ባጋጠሙ ተግዳሮቶች ምክንያት ያልተሳኩትን በብቃት በመፈተሽ በሃላፊነት ስሜት ለመፈጸም ስልጠናው ተደማሪ አቅም እንደሚሆን ተናግረዋል።
ሀገሪቱ አሁን ያለችበት ምዕራፍ ''ከእዳ ወደ ምንዳ'' የምንሸጋገርበት እና ዴሞክራሲን የማፅናት ምዕራፍ መሆኑንም አንስተዋል።
ለዚህም በየደረጃ ያለውን አመራር አቅም በመገንባት የጋራ አረዳድ ለመያዝ የሚያስችል ስልጠና መሆኑንም ገልጸዋል።
አመራሩ በዕውቀትና በክህሎት ዳብሮ በሀገሪቱ ያሉ ፀጋዎችን አውቆ በተሟላ ሁኔታ ወደ ብልፅግና ለመቀየር ለምናደርገው እንቅስቃሴ የማጠናከር ትጋት ይጠበቃል ብለዋል።
በቦንጋ ማዕከል ከ1 ሺህ በላይ የመንግስት ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች እየተሳተፉ ሲሆን ሥልጠናው እስከ ህዳር 12 ቀን 2016 ዓም እንደሚሰጥም ገልጸዋል።
ሀብትና ፀጋዎችን ማመንጨትና ማስተዳደር፣ ብሔራዊ አርበኝነትና ትርክትን በአግባቡ መገንባት፣ ድሎችና ውጤቶችን ማፅናት፣ ዘላቂ ሠላምን መገንባት የሚለውን ጨምሮ በስምንት ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ስልጠናው እንደሚሰጥም ጠቁመዋል።
ለሶስተኛ ዙር መሰጠት በጀመረው ስልጠና ላይ እንደ ሀገር በ17 ማዕከላት ወደ 22 ሺህ የሚጠጉ ሰልጣኞች እየተሳተፉ መሆናቸውንም አቶ ፀጋዬ ጠቁመዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የካፋ ዞን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው ።
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ፦
ፌስቡክ ገፃችንን
https://www.facebook.com/kfzgca
የቴሌግራም ቻናላችንን
https://t.me/ahkafaZGCAffairs ይወዳጁ ይከተሉ ይቀላቀሉ።