02/09/2024
የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ብልካ የስራ ርክክብ አደረጉ!
ነሃሴ-27/2016 ስልጤ ዞን ኮሙዩኒኬሽን:
የስልጤ ዞን ምክር ቤት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አድርጎ የሾማቸው አቶ ዘይኔ ብልካ ከቀድሞው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ከድር ጋር የስራ ርክክብ አድርገዋል።
አቶ ዘይኔ ብልካ ከቀድሞው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ከድር የስራ ርክክ በፈጸሙበት ወቅት ባደረጉት ንግግር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በልማትና በመልካም አስተዳደር የተያዙ ውጥኖችን ከዳር ለማድረስ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በዞን አስተባባሪዎች የተጀመረውን የሪፎርም ስራ በሁሉም መዋቅሮች በማካሄድ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ከዳር ለማድረስ በሚደረገው ጥረት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
የዞኑን ህዝብና ሌሎች አከባቢዎች የሚኖሩ የስልጤ ተወላጆችን አንድነት በስልጤ ልማት ማህበር አማካኝነት በማስተሳሰር የዞኑን ልማት ለማፋጠን የጀመሩ እንቅስቃሴዎችን በማጠናከር እንደሚሰራም አቶ ዘይኔ ተናግረዋል።
የዞኑን የኢንቨስትመንት አቅሞችን ማስተዋወቅና ባለሀብቶችን መሳብ፣በየደረጃው የተጀመሩ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ ማድረግ ሌላኛው የመንግስታቸው የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነም አቶ ዘይኔ አብራርተዋል።
አቶ ዘይኔ ብልካ በምክር ቤት እንደተሾሙ በዞኑ በጎርፍ የተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመጎብኘት ስራቸውን በይፋ መጀመራቸው የሚታወስ ነው።
የቀድሞው የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ከድር በበኩላቸው በቀጣይ የዞኑ አስተዳደር በሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።