Mensh Media

Mensh Media Media company

ከኦነግ ‘ሸኔ’ ጋር የሚደረገው ድርድር ያለ ስምምነት ተጠናቀቀ----በኦሮሚያ ክልል ያለውን ግጭት በማስወገድ ሰላምን ለማምጣት ያለመውና በታንዛኒያ ሲካሄድ የቆየው የሰላም ውይይት የመጀመሪያ ...
03/05/2023

ከኦነግ ‘ሸኔ’ ጋር የሚደረገው ድርድር ያለ ስምምነት ተጠናቀቀ
----
በኦሮሚያ ክልል ያለውን ግጭት በማስወገድ ሰላምን ለማምጣት ያለመውና በታንዛኒያ ሲካሄድ የቆየው የሰላም ውይይት የመጀመሪያ ምዕራፍ ዛሬ ሚያዚያ 25 ቀን 2015ዓም የተጠናቀቀ ቢሆንም ስምምነት ላይ አለመደረሱን የመንግስት ኮሙዪኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
ውይይቱ በአብዛኛው በአዎንታዊ መልኩ የተከናወነ ቢሆንም በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ግን በዚህኛው የውይይት ምዕራፍ ስምምነት ላይ ለመድረስ አልተቻለም። ግጭቱን በዘላቂነትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማስቆም እንዲቻል ሁለቱም አካላት የሰላም ውይይቱን መቀጠል አስፈላጊ መሆኑ ላይ መግባባታቸውን ተናግሯል።
በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትና እስካሁን ሲመራባቸው በነበሩ መሠረታዊ መርሖች መሠረት ግጭቱን በሰላማዊ መልኩ ለመፍታት መንግስት የጸና አቋም አለው። ይህንን መልካም አጋጣሚና በውይይት ችግሮችን የመፍታት በጎ ጅምር በመጠቀም ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ የኢትዮጵያ መንግሥት ያለውን ፅኑ አቋም ዳግም ያረጋግጣል ብሏል።

“መንግስት ኢንተርኔት በመዝጋት የሚያደርገውን አፈና ያቁም”-47 የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች----የጋዜጠኞች ተቆርቋሪ ተቋም የሆነው ሲፒጄን ጨምሮ 47 የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ...
03/05/2023

“መንግስት ኢንተርኔት በመዝጋት የሚያደርገውን አፈና ያቁም”-47 የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች
----
የጋዜጠኞች ተቆርቋሪ ተቋም የሆነው ሲፒጄን ጨምሮ 47 የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች መንግስት ኢንተርኔት በመዝጋት የሚያደርገውን አፈና ያቁም ሲሉ ለጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ጠየቁ። የጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት ያልተገደበ የኢንተርኔት እና የዲጂታል ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት የማግኘት መብትን ሊያረጋግጥ ይገባል ሲሉ ድርጅቶቹ በደብዳቤያቸው አሳስበዋል።
መንግስት ኢንተርኔትን በመዝጋት እንደመሳሪያ እየተጠቀመበት ይገኛል ሲሉ ስጋታቸውን በደብዳቤያቸው ያሰፈሩት ድርጅቶቹ ከቅርብ ግዜያት ወዲህ በሀገሪቱ አገልግሎቶቹ የተቋረጡበትን ሁኔታ በማሳያነት አቅርበዋል።
ኢንተርኔት አገልግሎትን መዝጋት መሰረታዊ የሰብአዊ መብትን መጋፋት እና የጋዜጠኞችን መብት እና ደህንነትን ማሳጣት ነው ሲሉ ድርጅቶቹ በደብዳቤያቸው ሞግተዋል።

የኤርትራ እና ከመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ውጭ ያሉ ታጣቂዎች ሙሉ በሙሉ ከትግራይ ለቀው እንዲወጡ አሜሪካ ጠየቀች----በፌደራል መንግስት እና በትግራይ ሀይሎች መካከል የተፈረመውን የሰላም ስም...
03/05/2023

የኤርትራ እና ከመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ውጭ ያሉ ታጣቂዎች ሙሉ በሙሉ ከትግራይ ለቀው እንዲወጡ አሜሪካ ጠየቀች
----
በፌደራል መንግስት እና በትግራይ ሀይሎች መካከል የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ስድስት ወራት መሙላቱን ተከትሎ የአሜሪካ የውጭ ዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን መግለጫ ሰጥተዋል። አንቶኒ ብሊንከን በመግለጫቸው በትግራይ የተጀመረው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን የኤርትራ እና ከመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ውጭ ያሉ ታጣቂዎች ሙሉ በሙሉ ከትግራይ ለቀው እንዲወጡ ጠይቀዋል። በተጨማሪም በፌደራል መንግስቱ እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል በታንዛንያ ድርድር መጀመሩን አወድሰዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባወጣው መግለጫ የፕሪቶርያው ስምምነት ተግባራዊነት ላይ ሁለቱም ሀይሎች ያሳዩትን ቁርጠኝነት አድንቋል። የመሰረታዊ አገልግሎቶች መጀመር፣ የሰብአዊ ረድኤት አቅርቦት መሻሻል፣ የህወሓት ሀይሎች ከባድ መሳሪያዎችን ማስረከባቸው፣ በእስር ላይ የነበሩ መለቀቃቸው፣ ሁሉን አካታች የሆነ የሽግግር ሂደት ለመከተል የተጀመረው ሂደት እና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መመስረቱን መስሪያቤቱ በመግለጫው ከጠቀሳቸው ውስጥ ይገኙበታል።

በአማራ ክልል ተነስቶ የነበረውን ውጥረት ተከትሎ ለእስር የተዳረጉ ሰባት ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ሲል አምኒስቲ ኢንተርናሽል አሳስቧል።----የጋዜጠኞቹ እስር የሚዲያ ነጻነት እና ሐሳብን...
27/04/2023

በአማራ ክልል ተነስቶ የነበረውን ውጥረት ተከትሎ ለእስር የተዳረጉ ሰባት ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ሲል አምኒስቲ ኢንተርናሽል አሳስቧል።
----
የጋዜጠኞቹ እስር የሚዲያ ነጻነት እና ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ላይ የተወሰደ ጥቃት ነው ያለው ድርጅቱ፤ ድርጊቱን የፈጸመው የሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋዜጠኞቹ በፍጥነት እንዲፈታ እና የቀረበባቸውን ክስ እንዲያነሳ ብሏል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ፤ ‹‹ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኀን ባለሞያዎች፣ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ፤ ለሕዝብ ተገቢውን መረጃ እንዲያደርሱ እና የመንግሥት ኃላፊዎችን ተጠያቂ ማድረግ እንዲችሉ፣ ሥራቸውን ያለምንም ስጋት፣ ጣልቃ ገብነት እና ትንኮሳ ሊሠሩ ይገባል።›› ብሏል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል አያይዞ ሦስት ወራት ያስቆጠረውና መንግሥት በተለያዩ ማኅበራዊ ሚድያዎች ላይ የጣለውን ማእቀብ እንዲያነሳና፤ የዜጎች ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ እና መረጃ የማግኘት መብትን እንዲያከብር ጥሪ አስተላልፏል።
(ዘገባው የአዲስ ማለዳ ነው )

በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ የተመራ የክልል ርዕሳነ መስተዳደሮች ልዑክ ወደ መቀሌ ገቡ----የሁሉም ክልል ርዕሰ መስተዳደሮቹ እና የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደ...
27/04/2023

በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ የተመራ የክልል ርዕሳነ መስተዳደሮች ልዑክ ወደ መቀሌ ገቡ
----
የሁሉም ክልል ርዕሰ መስተዳደሮቹ እና የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች በመቀሌ አሉላ አባነጋ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የመቀሌ ከተማ ነዎሪዎች ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የርዕሳነ መስተዳደሮቹ የመቀሌ ጉዞ ለትግራይ ክልል አጋርነታቸውን ለማሳየት እና በመልሶ ግንባታ ሂደት የድርሻውን ለማበርከት ዓላማ ያደረገ ነው።
የክልል ርዕሳነ መስተዳደሮች፣ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባዎች ወደ መቀሌ ሲያቀኑ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው::

የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ የብረት አጥር ዝርፊያን ለመግታት ኮንክሪት ለማድረግ መገደዱን አስታወቀ----የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በአዲሱ አዳማ ፈጣን መንገድ ዳርና ዳር የተተከለውን...
26/04/2023

የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ የብረት አጥር ዝርፊያን ለመግታት ኮንክሪት ለማድረግ መገደዱን አስታወቀ
----
የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በአዲሱ አዳማ ፈጣን መንገድ ዳርና ዳር የተተከለውን የብረት አጥር ዝርፊያ ለማስቀረት፣ የተተከሉትን የብረት አጥሮች በኮንክሪትና በተቀቀሉ እንጨቶች ለመቀየር መገደዱን አስታወቀ፡፡
በመንገዶቹ ዙሪያ የተተከሉትን ብረቶች ሊሰረቁ በማይችሉ አጥሮች ለመተካት ኢንተርፕራይዙ ጥናት ማድረጉን፣ በዚህም መሠረት የዕቃ ግዥ እየፈጸመ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የኢንተርፕራይዙ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙስጠፋ አባሰመል ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለስርቆት የተዳረጉትን ብረቶች በእንጨትና በኮንክሪት ለመቀየር በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
‹‹የመንገድ ላይ አጥር ቋሚ ብረቶቹን ኃላፊነት የማይሰማቸው ሰዎች ነቅለው በማይረባ ዋጋ ገበያ ውስጥ ሸጠው ለመጠቀም የሚያደርጉትን ተግባር ለመቀልበስ የተጀመረው ሥራ፣ ስርቆቱን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሰዋል፤›› ብለዋል፡፡ (ዘገባው የሪፖርተር ነው)

አበዳሪ አገሮች የኢትዮጵያን የዕዳ ሽግሽግ ሒደት በአፋጣኝ እንዲያገባድዱ የአውሮፓ ኅብረት ጠየቀ----ኢትዮጵያ አበዳሪ አገሮችን በተደጋጋሚ ስትጠይቅ ለቆየችው የዕዳ ይሸጋሽግልኝ ጥያቄ፣ አበዳ...
26/04/2023

አበዳሪ አገሮች የኢትዮጵያን የዕዳ ሽግሽግ ሒደት በአፋጣኝ እንዲያገባድዱ የአውሮፓ ኅብረት ጠየቀ
----
ኢትዮጵያ አበዳሪ አገሮችን በተደጋጋሚ ስትጠይቅ ለቆየችው የዕዳ ይሸጋሽግልኝ ጥያቄ፣ አበዳሪ አገሮች አፋጣኝ ምላሽ የመስጠት ሒደቱን እንዲያገባድዱ የአውሮፓ ኅብረት ጥሪ አቀረበ፡፡
አበዳሪ አገሮቹ በጋራ ባቋቋሙት የጋራ ማዕቀፍ ሥር የሚከናወነው የዕዳ ሽግሽግ የድርድር ሒደት፣ ‹‹አፋጣኝ መደምደሚያ›› ላይ እንዲደርስ አገሮቹ እንዲሠሩ ኅብረቱ እንደሚያበረታታ ገልጿል፡፡
በተጨማሪም ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የኢትዮጵያ መንግሥት የጀመረውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም እንዲደግፉ፣ ሚያዝያ 16 ቀን 2015 ዓ.ም. የኅብረቱ ምክር ቤት ያደረገውን ስብሰባ መጠናቀቅ አስመልክቶ በወጣው መግለጫ ጥሪ ቀርቧል፡፡
ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ያለባት የውጭ ብድር 28 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ 54 በመቶ የሚሆነው እንደ ዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ከመሳሰሉ የዓለም የፋይናንስ ተቋማት የተሰጠ ነው፡፡ ቀሪው 46 በመቶ ከአበዳሪ አገሮች የተገኘ ሲሆን፣ የቻይና ብድር ብቻ 25 በመቶ እንደሚሸፍን የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
(ዘገባው የሪፖርተር ነው)

የኢትዮጵያ ወታደራዊ ወጪ 88በመቶ ማደጉ ተገለጸ----በሲዊዲን ስቶኮልም የሚገኘው አለም አቀፉ የሰላም ጥናት ተቋም ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመላክተው ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2022 ለሚሊተሪ...
25/04/2023

የኢትዮጵያ ወታደራዊ ወጪ 88በመቶ ማደጉ ተገለጸ
----
በሲዊዲን ስቶኮልም የሚገኘው አለም አቀፉ የሰላም ጥናት ተቋም ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመላክተው ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2022 ለሚሊተሪ አንድ ቢሊየን ዶላር ወጪ አድርጋለች። ይህም ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር 88በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ተቋሙ አመላክቷል።
እንደ ተቋሙ መረጃ ከሆነ ጭማሪው የታየው ሀገሪቱ ባለፈው የፈረንጆቹ አመት ከትግራይ ሀይሎች ጋር ያደረገችው የእርስ በርስ ጦርነት ጋር የተገናኘ ነው።
በአጠቃላይ በአለም አቀፍ ደረጃ ባሳለፍነው የፈረንጆቹ አመት የነበረው ወታደራዊ ወጪ እጅግ ከፍተኛው መሆኑን ያመላከተው ተቋሙ የሀገራት ወታደራዊ ወጪ ባሳለፍናቸው ስምንት አመታት በተከታታይ የሶስት ነጥብ ሰባት በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን አስታውቋል። ከአለማችን ሀገራት መካከል ከፍተኛ ወታደራዊ ወጪ ያከናወኑ ሶስቱ ሀገራት አሜሪካ፣ ቻይና እና ሩሲያ መሆናቸውን የጠቆመው ተቋሙ የሶስቱ ሀገራት ወጪ የአጠቃላይ የአለም ሀገራትን 56 በመቶ እንደሚሸፍኑም ገልጿል።
(ዘገባው የአዲስ ስታንዳርድ ነው)

በርካታ ሀገራት ዜጎቻቸውን ከሱዳን ለማስወጣት የኢትዮጵያን መንግስት ትብብር በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ----ኢኮኖሚክ ታይምስ በድረገጹ እንዳስነበበው በርካታ ሀገራት ዜጎቻቸውን በአፋጣኝ ባለፉት ቀ...
25/04/2023

በርካታ ሀገራት ዜጎቻቸውን ከሱዳን ለማስወጣት የኢትዮጵያን መንግስት ትብብር በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ
----
ኢኮኖሚክ ታይምስ በድረገጹ እንዳስነበበው በርካታ ሀገራት ዜጎቻቸውን በአፋጣኝ ባለፉት ቀናት አስወጥተዋል።
አዲስ በተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለመጠቀም እና ዜጎቻቸውን ለማስወጣት ሀገራት ከወዲሁ ጥረት እያደረጉ ይገኛል። በጥረታቸው ውስጥ በተደጋጋሚ እየተነሳ የሚገኘው ደግሞ የኢትዮጵያ ስም ነው። ዜጎቻቸው በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሱዳን ያቀኑ ሀገራት ለማስወጣት በሚያደርጉት ጥረት የኢትዮጵያ መንግስት ትብብር እየጠየቁ እንደሚገኙ የየሀገራቱ መገናኛ ብዙሃን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።
የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዜጎቻቸውን ከሱዳን ለማስወጣት እና ወደ ቱርክ እንዲያመሩ ለማድረግ በሚቻልበት ጉዳይ ዙሪያ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ማውራታቸውን ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ አናዶሉ ዘግቧል።
የጋና መገናኛ ብዙሃን በበኩላቸው የሀገራቸው የውጭ ጉዳይ ባለስልጣናት በሱዳን የሚገኙ ጋናውያንን በኢትዮጵያ በኩል ለማስወጣት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ አስነብበዋል።
የሮማንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም በኢትዮጵያ በሚገኘው ኢምባሲው አማካኝነት ዜጎቹን ለማስወጣት እየጣረ እንደሚገኝ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
የኬንያ መንግስት አንድ መቶ የሚሆኑ በሱዳን ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ዜጎቹን በኢትዮጵያ በጎንደር በኩል ማስወጣቱን የሀገሪቱ ጋዜጦች ማስነበባቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
በሌላ በኩል በሱዳን ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ናይጀሪያውያን በሀገሪቱ የተፈጠረውን ቀውስ በመሸሽ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ዝግጅቶቻቸውን ማጠናቀቃቸውን እና በጉዳዩ ዙሪያ የናይጀሪያ መንግስት ባወጣው መግለጫ ተማሪዎቹ በቤታቸው እንዲቆዩ እና ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ማሳቡም ተዘግቧል።
(ዘገባው የአዲስ ስታንዳርድ ነው)

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ተማሪዎቹ በስልክ ሪፖርት እንዲያደርጉ አሳሰበ----በሰሜኑ ጦርነት ውድመት የደረሰበትና ከ35 ሺ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ የነበረው መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ከጦርነ...
25/04/2023

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ተማሪዎቹ በስልክ ሪፖርት እንዲያደርጉ አሳሰበ
----
በሰሜኑ ጦርነት ውድመት የደረሰበትና ከ35 ሺ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ የነበረው መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ከጦርነቱ በኋላ ስራ ለማስጀመር እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
በፌደራል መንግስት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል በነበረው ጦርነት ሳቢያ ለዓመታት የመማር ማስተማር ስራውን ያቋረጠው መቀሌ ዩኒቨርሲቲ አሁን የጥገና እና የመረጃ ማጣራት ስራዎችን እየሰራሁ ነው ብሏል።
የዩኒቨርሲቲው የትምህርት ክፍል ምክትል ኃላፊ ሳሙኤል ክፋሌ (ዶ/ር) ትምህርት ከመጀመሩ በፊት የጥገና፣ የበጀት ማስተካከል እና የአእምሮ ማነቃቂያ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል።
በሌላ በኩል ዩኒቨርስቲው ከጦርነቱ በፊት አንደኛ ዓመት የነበሩና ያቋረጡ ተማሪዎች በስልክ መረጃቸውን እንዲሰጡ ማስታወቂያ አውጥቷል። ከሚያዝያ 16 እስከ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ስም፣ የትምህርት ክፍልና ስንተኛ ዓመት እንደነበሩ በስልክ መግልጽ እንዳለባቸው ለተማሪዎች አሳስቧል።
በተጨማሪም በሌሎች ዩኒቨርስቲ ሲማሩ የነበሩ ተማሪዎችም ሲማሩበት የነበረውን ተቋም እንዲያሳውቁ አሳስቧል። የዩንቨርሲቲው ሰራተኞች ሪፖርት እንዲያደርጉ መመሪያ መዘጋጀቱን እና ለመልሶ ማደራጀት ስራው የሰርቪስ ተሽከርካሪዎች ጥገና እየተደረገላቸው ነው ተብሏል። ይሁን እንጂ ዩኒቨርሲቲው በትክክል ስራ የሚጀምርበት ቀንም ሆነ ወር አልተገለፀም።
(ዘገባው የአዲስ ዘይቤ ነው)

የአዲስ አበባ ተወላጆች በከተማዋ ካቢኔ ውስጥ ተሳትፏቸው እንዲጨምር ተጠየቀ---ጥያቄው የቀረበው፣ ‹‹ምክንያታዊ ወጣት ለአዲስ አበባ ብልፅግና›› በሚል መሪ ቃል፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳ...
25/04/2023

የአዲስ አበባ ተወላጆች በከተማዋ ካቢኔ ውስጥ ተሳትፏቸው እንዲጨምር ተጠየቀ
---
ጥያቄው የቀረበው፣ ‹‹ምክንያታዊ ወጣት ለአዲስ አበባ ብልፅግና›› በሚል መሪ ቃል፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሁሉም ክፍላተ ከተሞች ከተውጣጡ 16 ሺሕ የሚሆኑ ወጣቶች ጋር፣በሚሊኒየም አዳራሽ ውይይት ባደረገበት መድረክ ነው፡፡
በመድረኩ ወጣቶቹ ካቀረቧቸው በርካታ ጥያቄዎች መካከል በአዲስ አበባ ተወላጅ የሆኑ ምሁራን በፖለቲካ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ፣ እንዲሁም በከተማው የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ ሆነው ሕዝብን በማገልገል ረገድ ተሳትፏቸው ዝቅተኛ ነው የሚለው ይገኝበታል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የአዲስ አበባ ነዋሪ ማለት ተወላጅም፣ አዲስ አበባ ውስጥ የኖረም ነው፤›› በማለት፣ ከተወላጅ አንፃር ከታየ ከአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ ውስጥ ግማሽ የሚሆነው የከተማዋ ተወላጅ ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
‹‹እስከ አዲስ አበባ ምክትል ከንቲባነት ማዕረግ ድረስ ያሉ ኃላፊዎች የአዲስ አበባ ልጆች ናቸው፡፡ በነዋሪነትም ትናንት የመጡ የሚባለው ውሸት ነው፡፡ ስንመረጥም ጀምሮ ለሕዝቡ በደንብ ገልጸናል፡፡ ከ20 ዓመታት በታች የኖረ በጣም ጥቂት ሰው ነው፤›› በማለት ከንቲባዋ አስረድተዋል፡፡
ከንቲባዋ አክለውም፣ ‹‹ተሳትፎው በቂ አይደለም ሊባል ይችላል፣ ነገር ግን አለ፡፡ እኛም እንደ አንድ ትኩረት እያየነው ነው፤››› ብለዋል፡፡
(ዘገባው የሪፖርተር ነው)

12/04/2023

ገዥው ብልፅግና ፓርቲና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በወቅታዊው የአማራ ክልል ውጥረት ምክንያት ተፋጠዋል
----
የክልል ልዩ ኃይሎችን በአገር መከላከያ፣ በፌዴራል ፖሊስና በክልል ፖሊስ መዋቅሮች እንዲደራጁ ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ፣ በአማራ ክልል በተቀሰቀሰው ተቃውሞ፣ ገዥው ብልፅግናና አብን የቃላት ጦርነት ውስጥ ገብተዋል፡፡
ስድስተኛ ቀኑን የያዘውና በአማራ ክልል በርካታ ከተሞች በቀጠለው ተቃውሞ የክልሉ ነዋሪዎች ውሳኔው ጊዜውን ያልጠበቀ፣ የክልሉን የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያላስገባ ከመሆኑም በላይ፣ የክልል ልዩ ኃይል መፍረስ ውሳኔ በክልላቸው ቀድሞ መጀመሩ ቁጣ እንደቀሰቀሰባቸው በፖለቲከኞች ዘንድ በተደጋጋሚ ተወስቷል፡፡
አብን መጋቢት 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የገዥው ብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የክልል ልዩ ኃይሎችን በሚመለከት ያሳለፈው ውሳኔ፣ በሁሉም ክልሎች ልዩ ኃይሎች ላይ በእኩል ደረጃ ተፈጻሚ የማይሆንና የውሳኔው ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ የአማራ ልዩ ኃይልን ትጥቅ ማስፈታት መሆኑን ስለመገምገሙ አስታውቆ ነበር፡፡
ፓርቲው ከበቂ የሽግግር ጊዜ በኋላ የክልል ልዩ ኃይሎችን አደረጃጀት ማስተካከል እንደሚገባ የሚያምን መሆኑን ገልጾ፣ ጉዳዩን ከሕጋዊነት፣ ከወቅታዊና አገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎች አንፃር በመመርመር ገዥው ፓርቲ ያሳለፈው ውሳኔ ወቅቱን ያልጠበቀ እንደሆነ በመግለጫው አስታውቋል፡፡
አብን ክስተቱ ከተፈጠረ ወዲህ በተከታታይ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ይፋ ባደረጋቸው መግለጫዎች፣ ሕወሓት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተካሄደው የሰላም ስምምነት መሠረት ትጥቅ ባልፈታበት ልዩ ኃይልን ያለ በቂ ዝግጅት፣ ውይይት፣ የጋራ መግባባትና መተማመን ሳይደረስ በድንገትና ያለ በቂ የፀጥታ ዋስትና ለማፍረስ መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔና ውሳኔውን ለማስፈጸም እየሄደበት ያለው መንገድ ኃላፊነት የጎደለው ነው ብሏል፡፡
በተመሳሳይ ገዥው ፓርቲና የፌዴራሉ መንግሥት ስህተቱን ከማረምና መፍትሔ ከማፈላለግ ይልቅ፣ በጥፋት ላይ ጥፋት እየጨመረ ችግሩን እያወሳሰበና ክልሉን ለከፍተኛ አለመረጋጋትና የፀጥታ መደፍረስ እየዳረገው እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ በዚህም ሳቢያ በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች የተቃውሞ ሠልፎች ስለመካሄዳቸውና መደበኛ እንቅስቃሴዎች መስተጓጎላቸውን ጠቅሶ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች በከባድ መሣሪያ ጭምር የታገዘ ተኩስ በመኖሩ ይህ በአሰቸኳይ ይቁም ሲል ጠይቋል፡፡
አብን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከቀናት በፊት ጉዳዩን በተመለከተ፣ “ከጊዚያዊ መፍትሔ ዘላቂ ጥቅም አይገኝም” በሚል ርዕስ ባወጡት መግለጫ፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን ትጥቅ የማስፈታት ውሳኔ ‹‹ዋጋ ተከፍሎም ቢሆን ተግባራዊ እንደሚደረግና የሕግ ማስከበር ዕርምጃ እንደሚወሰድ›› ማለታቸው፣ በአማራ ክልል አለመረጋጋት እንዳይኖርና ለፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ነው ሲል አስታውቋል፡፡
ብልፅግና ፓርቲ ሰኞ ሚያዝያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹የአገራችን የፖለቲካ ተዋናያን ከሕገወጥና መርህ አልባ እንቅስቃሴ ሊቆጠቡ ይገባል፤›› ብሏል።ብልፅግና በመግለጫው አንዳንድ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችና መሪዎቻቸው፣ እንዲሁም ማኅበራዊ አንቂዎች ነን የሚሉ ግለሰቦች፣ ጉዳዩን አንድን ክልል ብቻ ትጥቅ የማስፈታት ጉዳይ አድርገው የሚያቀርቡበትና ጉዳዩን ለመግለጽ የሚጠቀሙባቸው፣ ‹‹ማክሰም፣ ማጠፍ፣ ማፍረስ፣ መበተን…›› የሚሉት አገላለጾች ምንጫቸው ከየትና ምርጫቸው እንዴት እንደሆነ፣ ግባቸውም ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስና ሕዝብን ለማሳሳት በመሞከር ጊዜያዊ ቅቡልነት ለማግኘት የመጣር ፍላጎት ነው ሲል አስታውሷል፡፡
በመሆኑም ከዚህ አገርን ዋጋ ከሚያስከፍል ሕገወጥና መርህ አልባ እንቅስቃሴ እንዲቆጠቡ በማሳሰብ፣ ‹‹ይህንን ውሳኔ በአማራ ክልል ላይ ብቻ የተወሰነ ውሳኔ አድርገው ለማቅረብ የሚጋጋጡ አገር ነቅናቂ ግጭት ናፋቂ ኃይሎች የሚነዙት መርዛማ መረጃ ፍጹም ሐሰት እንደሆነ ፓርቲያችን በአጽንኦት ማሳወቅ ይፈልጋል፤›› የሚለው የብልፅግና መግለጫ፣ ውሳኔው ሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ተነጋግረው የተወሰነ ብቻ ሳይሆን በተመሳሳይ የጊዜ መስመር በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የሚተገበር ስለመሆኑ አስታውቋል፡፡
‹‹የክልል ልዩ ኃይሎች ሕገ መንግሥታዊ በሆኑት የፀጥታ መዋቅሮች ገብተው እንዲያገለግሉ መደረግ እንዳለበት ከብልፅግና እኩል (አንዳንዴም በላይ) ሐሳብ ሲያነሱና ሲሞግቱ የነበሩ ፓርቲዎችና አመራሮችም ጭምር ዛሬ ላይ ከሥጋው ፆማለሁ ከመረቁ ስጡኝ ዓይነት መግለጫ ለማውጣት መጋጋጣቸው ፓርቲያችንን በእጅጉ አሳዝኖታል፤›› ብሏል፡፡
ብልፅግና በመግጫው ሻማ እንዲሸጥላቸው ጨለማ የሚናፍቁና የሚጠብቁ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎችና መሪዎቻቸው፣ ነገሮችን ከማባባስና ሞትን ለመጥመቅ ግጭት ከመጠንሰስ እንዲቆጠቡ በአፅንኦት አሳስባለሁ ሲል አስታውቋል፡፡
አብን ማክሰኞ ሚያዝያ 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የገዥው ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የልዩ ኃይልን ለማፍረስና ውሳኔውን ለማስፈጸም የወሰዳቸው ዕርምጃዎች፣ በአማራ ክልል ላስከተሉት ከፍተኛ አለመረጋጋት፣ የመደበኛ እንቅስቃሴዎች መስተጓጎልና ለፀጥታ መደፍረስ ምክንያት መሆኑን ገልጿል፡፡
ገዥው ፓርቲ ሚያዝያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ያወጣውን መግለጫ፣ ‹‹እውነታን የካደና አሁንም ገዥው ፓርቲ ለመፍትሔው ዝግጁ አለመሆኑን የሚያሳይ መሆኑን፣ ገዥው ፓርቲ ውሳኔው በአማራ ክልል ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በተመሳሳይ የጊዜ መስመር የሚተገበር ነው ቢልም፣ ከአማራ ክልል በቀር በየትኛውም ክልል የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላትን ትጥቅ የማስፈታት ወይም በገዥው ፓርቲ አነጋገር “መልሶ የማደራጀት” እንቅስቃሴ አልተደረገም፤›› ብሏል፡፡
በዚህም ገዥው ፓርቲ ሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የተስማሙበት ውሳኔ መሆኑን ሲናገር የቆየ ቢሆንም፣ የአማራ ክልልን ጨምሮ የየትኛውም ክልል ካቢኔ ወይም ምክር ቤት ጉዳዩን አስመልክቶ ያደረገው ውይይትም ሆነ ያሳለፈው ሕጋዊ ውሳኔ የሌለ መሆኑን አብን በመግለጫው ጠቁሟል፡፡
በስድስተኛው ምርጫ ተወዳድረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑ አምስት የአብን ተወካዮች ማክሰኞ ሚያዝያ 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ፣ ‹‹የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የክልል ልዩ ኃይሎች እንዲፈርሱ ያሳለፈውን ውሳኔ፣ በፌዴራል መንግሥት ስምና በመከላከያ ሠራዊት የኃይል ዕርምጃ ለማስፈጸም የሚያደርገውን ፋሽስታዊ ዕርምጃ ሊያቆም ይገባል፤›› ብለዋል፡፡
የአብን የፓርላማ አባላት በመግለጫቸው የብልፅግና ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መጋቢት 2015 ዓ.ም. የክልል ልዩ ኃይል አደረጃጀትን በተመለከተ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ አገሪቱ ከነበረችበት አንፃራዊ መረጋጋት፣ ሰላምና ተስፋ መፈንጠቅ ወደ ትርምስ፣ ሥጋትና የመበተን አደጋ ገብታለች ሲሉ በመግለጫቸው ገልጸዋል፡፡
የብልፅግና ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ ፓርቲው ሕገ መንግሥታዊ የመንግሥትና ሕዝብ ተቋማትን ‹‹እንደ ፓርቲው አደረጃጀት የቆጠረ፣ ለብቻው በፓርቲ ደረጃ በሕዝብና በመንግሥት ተቋማት ላይ አዛዥ ናዛዥ እንደሆነ አድርጎ ያቀረበ በመሆኑ ከሕግ፣ ከሞራልና ከአሠራር አንፃር ተቀባይነት የሌለው ነው፤›› ሲሉ አባላቱ በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የታጠቀ ኃይል ማንቀሳቀስ የማይችሉ መሆናቸውን የሚደነግገውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር የተመለከተውን አዋጅ ቁጥር 1162/2011 የተላለፈ መሆኑን ገልጸው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የብልፅግና ፓርቲን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሕግ የጣሰ ውሳኔ በመመርመር በፓርቲው ላይ ተገቢውን የሕግ ዕርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡
በአማራ ክልል እየተደረጉ ባሉ የተቃውሞ ሠልፎች የማኅበራዊ አገልግሎቶች የተቋረጡ ሲሆን፣ ከክልሉ ውጪ የትራንስፖርት አገልግሎቶች ተቋርጠዋል፡፡ የመከላከያ ሠራዊት በከተሞች ሥምሪት ማድረጉ የታወቀ ሲሆን፣ በአንዳንድ ከተሞች የመከላከያ ሠራዊት ከታጠቁ አካላት ጋር የተኩስ ልውውጥ ማድረጉና ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ዜጎች መገደላቸውና መቁሰላቸው እየተገለጸ ነው፡፡ (ዘገባው የሪፖርተር ነው)

12/04/2023

በደብረ ብርሃን መውጣትም መግባትም አልተቻለም
----
የክልል ልዩ ኃይሎችን እንደገና ማደራጀት ወይም ወደ መከላከያ፣ ፖሊስ፣ ፌዴራል ፖሊስ ለማካተት ወይም ወደ ሲቪል ለመመለስ ከተጀመረው እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ፣ በተለይ በአማራ ክልል ተቃውሞ መነሳቱ ይታወቃል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ከእሑድ ሚያዚያ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች ሰላማዊ ሠልፍ የተደረገ ሲሆን፣ የሪጂዮ ሜትሮ ፖሊቲያን ከተማ መሆኗ በምትታወቀው ደብረብርሃን ከተማ ግን ጉዳዩ ከረር ብሎ ቀጥሏል፡፡
በከተማው እሑድ ሚያዚያ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ውዥንብር እንደነበረ የከተማው ነዋሪዎች የገለጹ ሲሆን፣ በተለይ ከትናንት በስቲያ ሚያዚያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ሁሉም እንቅስቃሴ መቆሙን ተናግረዋል፡፡ አቶ ሰላሙ ተገኝ የተባሉ የደብረብርሃን ነዋሪ ለሪፖርተር እንደለጹት፣ ሰኞ ከሰዓት በኋላ ከከተማው መግቢያ ማለትም ከአዲስ አበባ ወደ ደብረብርሃን መግቢያ አካባቢ ወይም ዳሸን ቢራ ፋብሪካ አካባቢ የከባድ መሣሪያ ተኩስ ሲሰማ ነበር፡፡ የተኩስ ድምፅ የሚሰማው ከሁለት አቅጣጫ የሚመስል ሲሆን፣ ይህ ሁኔታ ሌሊቱን አድሮ ማክሰኞ ትናንት ሚያዚያ 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ተኩሱ ያለማቋረጥ መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡
እሳቸው እንደተናገሩት፣ ምክንያቱ የመከላከያ ሠራዊት ልዩ ኃይሎችን ትጥቅ ለማስፈታት ወደ ደብረብርሃን በመምጣቱ እንደሆነ መስማታቸውን ተናግረዋል፡፡
ሰሞኑን በተለያዩ የመረጃ መንገዶች የአማራ ክልል ልዩ ኃይልና ፋኖ ትጥቅ ሊፈቱ እንደሆነ ሲነገር በመክረሙ፣ በአካባቢው የሚገኙት የልዩ ኃይል አባላት ‹‹ለምን?›› በማለት ሳይቃወሙ እንዳልቀሩና መከላከያ መግባት የለበትም የሚል አቋም ይዘው እየተታኮሱ ሊሆን እንደሚችል ነዋሪው አስረድተዋል፡፡
የደብረብርሃን ከተማ ሰኞ ከሰዓት ጀምሮ ተቋማት፣ የንግድ ተቋማትና ሁሉም አገልግሎት ሰጪ ሥፍራዎች ዝግ መሆናቸውን ሪፖርተር ያነጋገራቸው የከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
ከእሑድ ሚያዚያ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ከደሴና አካባቢ ከተሞች ወደ ደብረብርሃን የሚገቡ የሰው ማመላለሻ አውቶቡሶች (ሽንኩርት፣ ሙዝ፣ ቅቤ፣ ጥራጥሬና ሌሎችም) የጫኑ አይሱዙዎችና ሌሎችም ተሽከርካሪዎች በተለምዶ ደብረብርሃን መውጫ (አስመራ በር) እና ወደ አንኮበር መገንጠያ መንገድ አንስቶ እስከ ቀይት፣ ባቄሎና ጣርማበር ድረስ መቆማቸውን ተናግረዋል፡፡ የጫኗቸው ሸቀጣ ሸቀጦች የሚበላሹም ስላሉባቸው ሊበላሹ እንደሚችሉም አክለዋል፡፡ ለተለያዩ ጉዳዮች ከአዲስ አበባ ወይም ከደሴና ሌሎች ከተሞች ተነስተው በመንገድ ላይ የቀሩት ተሳፋሪዎችም፣ ገንዘብ ያለው በእግር ወደ ደብረብርሃን መግባቱንና የሌለው በተሳፈረበት መኪና ውስጥ መሆኑንም አክለዋል፡፡
ችግሩ ጠንከር ያለ መሆኑን መንግሥት ተገንዝቦ ነገሮችን በኃይልና በእልህ ሳይሆን በመነጋገርና በመወያየት መፍታት እንዳለበት ጠቁመው፣ ያ የማይሆን ከሆነ ግን ለአገርም ሆነ ለወገን የሚፀፅት ነገር ሊከሰት እንደሚችል ሥጋታቸውን ተናግረዋል። በተያያዘ ዜናም በአጣዬ ከተማና ዙሪያው ከፍተኛ ተኩስ መኖሩና በተለይ ሴቶችና ሕፃናት አካባቢውን ለቀው መውጣታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እየገለጹ ነው፡፡ በአጣዬ ከተማ የመከላከያ ሠራዊት መኖሩን ጠቁመው ሁኔታው ግን እንደሚያስፈራና ተጨማሪ ኃይል ሳያስፈልግ እንደማይቀር ግን ሥጋታቸውን አክለዋል፡፡ (ዘገባው የሪፖርተር ነው)

12/04/2023

“በኢትዮጵያ ያለውን የሁለትዮሽ የውጭ ምንዛሪ ገበያ እንዳይቀጥል” ዓለም ባንክ እና አይ.ኤም.ኤፍ
----
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍና ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ያለውን የሁለትዮሽ የውጭ ምንዛሪ ገበያ እንዳይቀጥል ለማድረግ የሚያስችል መፍትሔ ለማግኘት በዚህ ሳምንት ስብሰባ ሊቀመጡ መሆናቸውን ገለጹ፡፡
ስብሰባው በዚሁ ሳምንት መካሄድ በጀመረው የሁለቱ ተቋማት ዓመታዊ የስፕሪንግ ጉባዔ (Spacing Meetings) ጎን ለጎን እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱና የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴን ጨምሮ የኢትዮጵያ ልዑክ ጉባዔውን ለመካፈል በዋሽንግተን ይገኛሉ፡፡
ሰኞ ሚያዝያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ዴቪ ማልያስና የአይኤምኤፍ ዋና ዳይሬክተር ባደረጉት የጋራ ውይይት፣ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ካሉበት ውስብስብ ችግሮች እንዴት መውጣት እንደሚችሉ ከጉባዔው መፍትሔ ሊገኝ ይችላል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
‹‹በኢትዮጵያ ያለው የሁለትዮሽ የምንዛሪ ገበያ ትልቅ ማነቆ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ሕጋዊው የምንዛሪ ገበያ ጥቂቶችን ብቻ ነው የሚያገለግለው፡፡ ሕገወጥ የሆነው የትይዩ ገበያ ደግሞ በጣም ውድ ስለሆነ እሱም ጥቂቶችን ያገለግላል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ምንዛሪ ገበያ ውጤታማ ሊሆን አልቻለም፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት በዚህ ሳምንት በጠረጴዛ ዙሪያ እንሰባሰባለን፤›› ሲሉ ዴቪድ ማልያስ ገልጸዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት በኢትዮጵያ ካለው 120 ሚሊዮን ሕዝብ አብዛኛው በሁለትዮሽ ገበያ ሥርዓት ምክንያት እየተጎዳ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተሾሙ አራት ዓመታት ያለፋቸው ማልያስ እ.ኤ.አ. 2019 ኢትዮጵያ መጥተው የነበረ ሲሆን፣ በዚያው ዓመት የአይኤምኤፍ ዋና ዳይሬክተር ክርስቲና ጅዮርጅዮሽም ኢትዮጵያን ጎብኝተው ነበር፡፡
የዕዳ ሽግሽግንም በተመለከተ ተጨባጭ ውሳኔ ከዚህ ጉባዔ እንደሚጠበቅ ኃላፊዎቹ ጠቁመዋል፡፡ ሁሉም አብዳሪዎች ከተበዳሪዎች ጋር ለመጀመርያ ጊዜ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ እንደሚመክሩ ተነግሯል፡፡ ስብሰባው (ጉባዔው) ከሰኞ እስከ እሑድ ይደረጋል፡፡
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በአይኤምኤፍ አማካሪነት ሀብታም አገሮችና ሌሎች አበዳሪዎች ሊያደርጉ ከተስማሙት የታዳጊ አገሮች ዕዳ ሽግሽግ ተጠቃሚ ለመሆን የሁለትዮሽ ምንዛሪ ገበያውን አንድ ማድረግ (Currency Unification) እንዳለባት እንደ ቅድመ ሁኔታ ተጠይቋል፡፡
ሕጋዊውን የምንዛሪ ገበያና የትይዩ ገበያን አንድ ለማድረግ የብርን የመግዛት አቅም አሁን ካለበት ቢያንስ በእጥፍ በማወረድ (Devaluation) የጥቁር ገበያው አሁን ካለበት እኩል ማድረግ ግዴታ መሆኑን፣ ሁለት ተቋማት ሲወተውት እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ሁለት ሳምንታት አዲስ አበባ የከረሙት የአይኤምኤፍ የባለሙያ ቡድን፣ ይህንን አቋም አጠናክሮ ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሲገለጽ መቆየቱን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡
‹‹አይኤምኤፍና ዓለም ባንክ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አላት ብለው አያስቡም። ችግሩ የምንዛሪ አስተዳደሩ ነው ብለው ይደመድማሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክራቸው የብርን የመግዛት አቅም እንደገና በማውረድ የጥቁር ገበያው ምንዛሪ አሁን ካለበት እኩል ማድረግ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ጥቁር ገበያው አሁን ካለበት አማካይ 100.00 ብር አካባቢ) ከፍ እያለ ለመሄድ አይችልም ወይም ረዥም ጊዜ ይወስድበታል ብለው ያስባሉ፤›› ይላል ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የምጣኔ ሀብት አማካሪ፡፡
ውሳኔው በተተገበረበት ብሔራዊ ባንክ ባለፉት ዓመታት በቁጥቁጥ ሳያወርድ የነበረውን የብር የመግዛት አቅም በቅርቡ ያንሸራትታል ይላሉ አማካሪ፡፡
ይሁን እንጂ ይህ ውሳኔ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲመጣ ማድረግ ቢችልም፣ የጎንዮሽ ጉዳቱ ግን የገቢ ምርቶችን ማስወደድና በኢትዮጵያ ያለውን የዋጋ መናር ማባባስ ነው ይላሉ፡፡
የሳምንታት ቆይታቸውን ባለፈው ቅዳሜ ያጠናቀቁት የኤይኤምኤፍ የባለሙያዎች ቡድን ባወጡት አጭር መግለጫ፣ የአገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ቁጥር ሁለትን ለመደገፍ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡ በረቂቅ ደረጃ ያለው ሁለተኛው የአገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ዶክመንት የምንዛሪ ገበያው ቀስ በቀስ መከፈቱ (Liberalize) እንዳለበት ይጠቁማል፡፡ (ዘገባው የሪፖርተር ነው)

12/04/2023

“ልዩ ኃይሎችን በማደራጀት ሂደት የሚፈጸም ሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ይቁም” ኢሰመጉ
----
የክልል ልዩ ኃይሎችን ለማደራጀት እየተከናወነ ባለው እንቅስቃሴ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መንግሥት እንዲያስቆም፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ማክሰኞ መጋቢት 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ጠየቀ።
መንግሥት መጋቢት 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ መሠረት፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለመጠበቅ የሚያስችል አንድ ጠንካራ የተማከለ ሠራዊት ለመገንባት አቅጣጫ በማስቀመጥ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የልዩ ኃይል አባላት እንደ ምርጫቸው በመከላከያ፣ በፌዴራል ፖሊስና በክልል ፖሊስ አባልነት መካተት እንደሚችል መግለጹን ያስታወሰው ኢሰመጉ፣ ‹‹ከዚህ ጋር ተያይዞ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች ከመንግሥት እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ በአፈጻጸም ተገቢነት ላይ የተለያዩ ግንዛቤ በመኖሩ ምክንያት፣ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ድርጊቱን በመቃወም ሠልፍ የተደረገ ሲሆን፣ እነዚህንም ሠልፎች ተከትሎ መንገዶች መዘጋታቸውንና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን ከአካባቢው ካሰባሰባቸው መረጃዎች መረዳት ችያለሁ፤›› ብሏል፡፡
ኢሰመጉ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለመንግሥት ባደረገው ጥሪ፣ ‹‹ይህ በመንግሥት እየተወሰደ ያለው የልዩ ኃይል አባላትን መልሶ የማደራጀት እንቅስቃሴ በሌሎች ክልሎች እኩል ተፈጻሚነት ያለው በመሆኑ፣ ተመሳሳይ ሁኔታዎች እንዳይገጥሙ አካሄዱንና ምክንያቱን አስመልክቶ ኅብረተሰቡን ያማከለና ግልጽ ሊሆን ይገባል፤›› በማለት አሳስቧል፡፡
‹‹ይህንን ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የሌለውን አደረጃጀት በሕግ ማዕቀፍ በተደገፈና አገራዊ መልክ ያለው አደረጃጀት መዘርጋት የሚደገፍ ተግባር ቢሆንም፣ ከአፈጻጸም ጋር ተያይዞ ልዩ ልዩ ባለድርሻ አካላትና በአጠቃላይ ለማኅበረሰቡ እንቅስቃሴውን ግልጽ ማድረጉ ለሚፈጽመው ተግባር ቅቡልነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፤›› ሲል ኢሰመጉ በመግለጫው ጠቅሷል፡፡
በመንግሥት እየተወሰደ ያለው የልዩ ኃይል አባላትን መልሶ የማደራጀት እንቅስቃሴ የክልሎችን ነባራዊ ሁኔታ፣ እንዲሁም ሥጋት ከግምት ውስጥ ያስገባ ሊሆን እንደሚገባ፣ መልሶ የማደራጀት እንቅስቃሴው የዜጎችን ደኅንነት ሥጋት ላይ የማይጥልና ከመልሶ ማደራጀት እንቅስቃሴው ጋር ተያይዞ ሥጋት ውስጥ የሚወድቅ ወይም ደኅንነቱ አደጋ ውስጥ የሚወድቅበት አካል ሊኖር እንደማይገባ የገለጸው ኢሰመጉ፣ ‹‹ስለሆነም መንግሥት ይህንን መልሶ የማደራጀት እንቅስቃሴ በሚከውንበት ወቅት ከላይ ለተጠቀሱት ነጥቦች ተገቢውን በቂ ትኩረት በመስጠት ከሥጋት የፀዳ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያን ፀጥታና ሰላም ዜጎችን ደኅንነት የሚጠብቅና ሰብዓዊ መብቶች የሚከበሩበት አገራዊ ግንባታ ላይ ያተኮረ መሆን አለበት፤›› ሲል አሳስቧል፡፡
ኢሰመጉ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባወጣው መግለጫ፣ መንግሥት እያካሄደ ያለውን የልዩ ኃይል አባላትን መልሶ የማደራጀት እንቅስቃሴ ለባለድርሻ አካላትና ለአጠቃላይ ማኅረሰቡ ግልጽና በምክር ላይ የተመሠረተ በማድረግ፣ ይህንን እንቅስቃሴ በሰላማዊ መንገድ በትዕግሥትና ዘላቂ ሕጋዊ መፍትሔ ከማምጣት አንፃር እንዲፈጸም፣ የልዩ ኃይል አባላትን መልሶ የማደራጀት እንቅስቃሴው ጋር ተያይዞ እየተፈጸሙ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዲያስቆምና መሰል ጥፋቶች እንዳይፈጸሙ ተገቢውን ትኩረትና ጥንቃቄ ሰጥቶ እንዲሠራ ጠይቋል፡፡
የፌዴራል እንዲሁም የሚመለከታቸው የክልል መንግሥታት ለጉዳዩ ሰላማዊ፣ ዘላቂና የማኅበረሰቡን ደኅንነትና ጥበቃ የሚያረጋግጡ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጡ ያሳሰበው ኢሰመጉ፣ ‹‹ማንኛውም ሰው ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ መብቱን፣ ሐሳቡን በነፃነት የመግለጽ መብቱን የሌላውን መብት ባልጣሰና በሕግ አግባብ እንዲለማመድ፣ እንዲሁም መንግሥት ሰዎች እዚህን መብቶች እንዲጠቀሙ ያላግባብ ገደቦችን እንዳይጥል፤›› ሲልም አሳስቧል፡፡
ኢሰመጉ አክሎም፣ ‹‹መንግሥት ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ የተዘጉ መንገዶችን በማስከፈት የዜጎችን የመዘዋወር መብት እንዲያስከብር፣ ኅብረተሰቡ፣ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት፣ የሲቪል ማኅበራትና የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በውጭ የሚኖሩ የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ ጋዜጠኞችና ልዩ ልዩ የሚዲያ አውታሮች፣ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በሙሉ ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ነገሮች እየተባባሱ ሄደው ለከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይዳረጉ ነገሮችን በትዕግሥትና በማስተዋል አገራዊ አንድነትና ሰላምን ለመገንባት በሚያስችል መንገድ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ በክልሎች የአካባቢያዊ ሰላምና ፀጥታ ለማስከበር በሚል የክልል ልዩ ኃይል አደረጃጀት በመዘርጋት እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ እንደቆዩ በመግለጫው የጠቀሰው ኢሰመጉ፣ ‹‹ሆኖም በእነዚህ ምክንያት በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በሰሜኑ ክፍል ከፍተኛ ቀውስ ያስከተለባቸው ጊዜዎች የቅርብ ትውስታዎቻችን ናቸው፡፡ ይህ አደረጃጀት ጅማሬው ሰላምና ፀጥታ የማስከበር እንቅስቃሴ ቢሆንም በተደጋጋሚ በማኅበረሰብ አንቂዎች፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በጋዜጠኞች፣ በውጭ አገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሕገ መንግሥታዊ መሠረት እንደሌለውና አስፈላጊ አለመሆኑ ሲጠቀስ ቆይቷል፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ክልሎች ልዩ ኃይሎቻቸውን በከፍተኛ ሁኔታ በማደራጀት በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ለሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት መሆናቸው የሚታወስ ነው፤›› ሲል በመግለጫው አክሏል፡፡ (ዘገባው የሪፖርተር ነው)

12/04/2023

ከኮንዶሚኒዬም ዕጣ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ “ከባድ የሙስና ወንጀል” ክስ የተመሰረተባቸው አምስት ግለሰቦች በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነጻ ተባሉ
----
የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክ ሙያና ስልጠና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሙሉቀን ሀብቱን ጨምሮ፤ ከኮንዶሚኒዬም ዕጣ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ “ከባድ የሙስና ወንጀል” ክስ የተመሰረተባቸው አምስት ግለሰቦች በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነጻ ተባሉ። በዚሁ መዝገብ ክስ ከቀረበባቸው ግለሰቦች መካከል አንድ ተከሳሽ በሌሉበት ጥፋተኛ ሲባሉ፤ ቀሪ አምስት ተከሳሾች ደግሞ የተከሰሱበት ድንጋጌ ተቀይሮ እንዲከላከሉ በፍርድ ቤቱ በይኗል።
ይህን ብይን የሰጠው ዛሬ ረቡዕ ሚያዚያ 4፤ 2015 የዋለው፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ችሎት ነው። ችሎቱ አምስት ተከሳሾችን በነጻ ያሰናበተው፤ “ዐቃቤ ህግ ባቀረበው የሰው እና የሰነድ ማስረጃ፤ ወንጀሉን በበቂ ሁኔታ ባለማስረዳቱ” መሆኑን ገልጿል። በነጻ ከተሰናበቱት ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ የቴክኒክ ሙያና ስልጠና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ የነበሩት አቶ አብርሃም ሰርሞሎ እና የከተማይቱ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ቢሮ የአይሲቲ ዳይሬክቶሬይትን ሲመሩ የነበሩት አቶ ኩምሳ ቶላ ይገኙበታል። (ዘገባው የኢትዮጵያ ኢንሳይደር ነው)

12/04/2023

በጦርነቱ የተሳተፉ ቤተሰቦቻቸውን ማግኘት እንደሚፈልጉ የመቀሌ ነዋሪዎች ተናገሩ
----
በትግራይ ኃይሎች እና በፌደራል መንግስት መካከል በተካሄደው ጦርነት በፍላጎትና በግዴታ በጦርነቱ የተሳተፉ ቤተሰቦቻቸውን ማግኘት እንደሚፈልጉ የመቀሌ ነዋሪዎች ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል
አቶ ገብረመስቀል አበበ የተባሉት ሌላኛው ነዋሪም የአንድ ወንድ ልጅ አባት ሲሆኑ “ከአንድ ቤት አንድ ሰው ወደ ጦርነት መግባት አለበት፣ ካልሆነ እርዳታ አይሰጠውሙ” በተባለ ጊዜ አንዱ ልጃቸው በግዳጅ ወደ ውጊያ ማምራቱን በሀዘን ድባብ ውስጥ ሆነው ነግረውናል።
አሁን በተደረሰው ስምምነት መሰረት “ልጄ ከዛሬ ነገ ይመጣል እያልኩ በሀዘንና በተስፋ እገኛለሁ” የሚሉት አቶ ገብረመስቀል ልብ በሚሰብር ሁኔታ እያለቀሱ ልጄ ካለ መንግስት ምላሽ ይስጠኝ ሲሉ ይማፀናሉ።
ወ/ሮ ለምለም ኃይሉ የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ናቸው። ለሁለት ዓመታት በቆየው ጦርነት ሁለት ልጆቻቸው ወደበረሃ ወርደው ጦርነቱን እንደተቀላቀሉ ይገልፃሉ። ጦርነቱ በሰላም ስምምነት ተቋጭቶ ግልፅነት ይጎድለዋል የሚሉ አካላት ቢኖሩም አንፃራዊ ሰላም ሰፍኖ ክልሉም ጊዜያዊ አስተዳደር ተሹሞለታል።
ይሁን እንጂ ወ/ሮ ለምለም ሁለት ልጆቻቸው እስካሁን ድረስ የት እንዳሉ እንደማያውቁ ገልፀው የልጆጃቸውን መገኛ በጉጉት እንደሚጠብቁ ነግረውናል። ከቤት በወጡበት ሰሞን ልጆቻቸው ደብዳቤ ይሉኩላቸው እንደነበር ለአዲስ ዘይቤ የተናገሩት አዛውንቷ፣ ለመጨረሻ ጊዜ የልጆቻቸውን ወሬ ከሰሙ 1 ዓመት ከ8 ወር ማለፉንም ገልፀዋል።
ወ/ሮ ለምለም ኃይሉ እንደሚናገሩት “ልጆቼን ለመፈለግ ያልደረሱስኩበት ቦታ የለም፣ መረጃ ላገኝ ግን አልቻልኩም” ብለው ወ/ሮ ለምለም ልብ በሚሰብርና ተስፋና ፍራቻ በተቀላቀለበት ሁኔታ ስለልጆቻቸው ይጠይቃሉ።
በተመሳሳይ የመቀሌ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ሃረግ ተሰማ በተፈጠረው ጦርነት የአራት ልጆቿ አባት ወደ ጦርነት መቀላቀሉን ትገልፃለች። ባለቤቷ አቶ ግርማይ ፈቃዱ በመምህርነት እየሰራ ልጆቹንና ቤተሰቦቹን ያስተዳድር ነበር።
ጦርነቱ ከጀመረ በኋላ በ2013 ዓ.ም. ከቤት እንደወጣ ወጣ እስካሁን ድረስ አድራሻው አይታወቅም። ወ/ሮ ሃረግ አሁን ላይ የቀን ስራ እየሰራች ልጆቿን ለማስተዳደር ተገድዳለች። “ስራ ካልተገኘ ደግሞ ቤቴ ነው የምውለው፣ ልጆችን ማስተዳደር ከባድ ነው” የምትለው የመቀሌ ከተማ ነዋሪዋ ለመጨረሻ ጊዜ የቤት ኪራይ ከከፈለች 2 ዓመታት ከግማሽ ስለማለፉ እንባ እየተናነቃት ነግራናለች። የባለቤቷ የት እንዳለ አለመታወቅ ለራሷ እና ለልጆቿ ሃዘን እንደሆነባቸውም ለአዲስ ዘይቤ ተናግራለች።
ሌላኛዋ የመቀሌ ነዋሪ ወይዘሮ ክንደሓፍቲ ባለቤታቸው በ2013 ዓ.ም ልጃቸው ደግሞ በ2014 ዓ.ም ለጦርነቱ ከቤት እንደወጡ እስካሁን በህይወት ስለመኖራቸውም ሆነ ስለመሞታቸው ምንም ወሬ የለም ይላሉ። “ያልሄድኩበትና ያልጠየቅኩበት ቦታ የለም” የሚሉት ወ/ሮ ክንደሓፍቲ አሁን ላይ መንግስት የት እንዳሉ ምላሽ ቢሰጠን ሲሉ በሀዘን ተናግረዋል። (ዘገባው የአዲስ ዘይቤ ነው)

10/04/2023

የክልል ልዩ ሃይል መፍረስ ላይ ህዝብ ሊመክርበት ይገባል ተባለ.....
የፌዴራል መንግስት የክልል ልዩ ሃይል አባላት ወደ መከላከያ ሰራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ፣ መደበኛ ፖሊስ እና ሲቪል መሆን እንደሚችሉ ማስታወቁን ተከትሎ በአማራ ክልል ውጥረት ተከስቷል።

ከዚህ ውሳኔ ጋር በተገናኘ በአማራ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች መንገድ መዝጋትን ጨምሮ የተኩስ ልውውጦች መኖራቸውን ዘግገቡ ይታውሳል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ አዲስ ዘይቤ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች አስተያየት ሰጪዎችን አነጋግራልች፡፡

የባህር ዳር ከተማ ኗሪ እና የመንግስት ሰራተኛ የሆኑት ግለሰብ በሰጡት አስተያየት ጉዳዩን በማህበራዊ ሚዲያ መስማታቸውን ገልፀው የሀገሪቱን ብሎም የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያላስገባ ውሳኔ ነው ይላሉ።
ልዩ ሀይል ይፍረስ የተባለበትን ውሳኔ “ተግባራዊ ማድረግ አስቸጋሪ ነው፤ ምክንያቱም የፌደራል መንግስት በየክልሎች ያለውን የልዩ ሀይል ብዛት እና የትጥቅ አቅም ሙሉ መረጃ ያለው አይመስለኝም” ይላሉ። ስለሆነም አንዱ ክልል ትጥቅ ፈቶ ሌላው ላይፈታ የሚችልበት እድል የሰፋ እንደሆነ ይገልፃሉ።

የክልሎችን ልዩ ኃይል የማፍረስ አጀንዳ በመንግስት ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ህብረተሰቡ ሊመክርበት ይገባል ይላሉ።

እንደ አስተያየት ሰጪዎች ማብራሪያ ልዩ ሀይል ትጥቅ ይፍታ የሚል ውሳኔ ሀገሪቱ እንዳትረጋጋ ሊያደርግ ስለሚችል በጥንቃቄ ሊታይ ይገባል ብለዋል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር በሰጡን አስተያየት በመጀመሪያ በክልሎች ያለው ልዩ ሀይል ብዛትና መጠን ሊለያይ ቢችልም በአዋጅ የተቋቋመ በመሆኑ በአንድ ፓርቲ ውሳኔ ሊፈርስ አይገባውም ብለው “ሂደቱ በራሱ ህግን የተከተለ” አለመሆኑን ያነሳሉ።

የጎንደር ከተማ ነዋሪየሆኑት የ78 ዓመት አባወራ “የአማራ ልዩ ሃይል እና ፋኖ ትጥቅ እንዲፈቱ እና ወደ ሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ ፌደራል ፖሊስና የከተማ ፖሊስ እንዲቀላቀሉ መደረጉ ለሃገር ዘለቂ ሰላም መስፈን ታስቦ እንጂ አማራ ክልልን ብቻ ለመጉዳት” እንዳልሆነ ይገልፃሉ።

የውጭ ሃገራትን ስንመለከት "ከእኛ የተሻለ ሰላም ሰፍኖ የሚታይባቸው አንድ የተደራጀ የፀጥታ አካል ብቻ በመኖሩ ነው" የሚሉት የጎንደር ነዋሪ፤ “ልዩ ሃይሉ ትጥቅ አንፈታም ማለታቸው ተገቢ” እንዳልሆነ በመግለፅ መንግስት ቃል እንደገባው ወደ መከላከያ፣ ፌደራልና የከተማ ፖሊስ ካልቀላቀላቸው እና መቀላቀል የማይፈልጉትን ሃይሎች መቋቋሚያ ሰጥቶ ወደ ሲቪል መቀየር ካልተቻለ ግን የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች መንግስትን የምንቃወም ይሆናል" ብለውናል።
(ዘገባው የአዲስ ዘይቤ ነው )

10/04/2023

እናት ፓርቲ፤ ዶ/ር ሰይፈ ሥላሴ አያሌውን ፕሬዝዳንት አድርጎ መረጠ
.....
እናት ፓርቲ፤ ዶ/ር ሰይፈ ሥላሴ አያሌውን ፕሬዝዳንት አድርጎ መርጧል፤ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑትን ጥሩማር አባተን ደግሞ ምክትል ፕሬዝዳንት አድርጎ መረጠ። ፓርቲው መጋቢት 30፤ 2015 ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤው፤ የተሻሻለውን የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ፣ አደረጃጀቱን የሚወስነውን ሰነድ እና የአምስት ዓመት ዕቅድም አጽድቋል።
ለስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ከፍተኛ ዕጩዎችን በማቅረብ በሶስተኛ ደረጃ ተቀምጦ የነበረው እናት ፓርቲ፤ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ሊያካሄድ የነበረው ከአንድ ወር ገደማ በፊት የካቲት መጨረሻ ላይ ነበር። በአዲስ አበባ አራት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው የቅድስት ስላሴ ዩኒቨርሲቲ አዳራሽ ሊካሄድ የነበረው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ፤ “ከበላይ አካል መጣ” በተባለ ትዕዛዝ ምክንያት መከልከሉ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰጠው መግለጫ፤ የእናት ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ የተደናቀፈው ለጊዜው ስሙን ለይቶ ባላረጋገጠው “የህግ አስፈጻሚ ኃላፊ ትዕዛዝ” መሆኑን አስታውቆ ነበር። ምርጫ ቦርድ በዚሁ መግለጫው፤ የእናት ፓርቲን ጨምሮ የሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤን ያሰናከሉ የህግ አስፈጻሚ አካላት ላይ ፍትሕ ሚኒስቴር ክስ እንደሚሰርት ይፋዊ ጥያቄ ማቅረቡም አይዘነጋም።
ትላንት በተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ፤ እናት ፓርቲን በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ የተመረጡት ዶ/ር ሰይፈ ሥላሴ የፖለቲካ ተሳትፏቸውን የጀመሩት በዚሁ ፓርቲ ውስጥ ነው። ከመጀመሪያ እስከ ዶክትሬት ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ ትምህርት ዘርፍ በሩስያ የተከታተሉት ዶ/ር ሰይፈ ስላሴ፤ አብዛኛውን የስራ ጊዜያቸውን ያሳለፉት በመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ነው።
(ዘገባው ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

10/04/2023

መስከረም አበራ ለሶስተኛ ጊዜ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለች.....
የ "ኢትዮ ንቃት” ዩ-ቲዩብ ሚዲያ መስራች እና ባለቤት የሆነችው መስከረም አበራ፤ ሚያዝያ 1 አመሻሽ ላይ በፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ስር መዋሏን ባለቤቷ አቶ ፍጹም ገብረ ሚካኤል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። መስከረም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለእስር ስትዳረግ የዛሬው ለሶስተኛ ጊዜ ነው።
በራሷም ሆነ በሌሎች መገናኛ ብዙኃን በምታቀርባቸው የፖለቲካ ትንታኔዎች ይበልጥ የምትታወቀው መስከረም፤ በአዲስ አበባ ጎሮ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቷ በቁጥጥር ስር የዋለችው 10 በሚሆኑ የፌደራል ፖሊስ አባላት መሆኑን አቶ ፍጹም ገልጸዋል። መስከረም በቁጥጥር ስር ከመዋሏ በፊት፤ በመኖሪያ ቤታቸው 50 ደቂቃዎች ገደማ የወሰደ “ብርበራ” መደረጉን ባለቤቷ ተናግረዋል።

ሲቪል እና የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ “የታጠቁ” የጸጥታ አካላት፤ መጀመሪያ “ለፍተሻ ነው የመጣነው” ሲሉ መናገራቸውን አቶ ፍጹም አስታውሰዋል። “የፍርድ ቤት ማዘዣ ይዛችኋል ወይ?” የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን የሚያነሱት አቶ ፍጹም፤ ሆኖም የፌደራል ፖሊስ አባላቱ “በemergency ጊዜ ፍተሻ ይደረጋል። እኛ ደግሞ የፌደራል ፖሊስ አባላት ነን። መታወቂያም ማሳየት እንችላለን” ሲሉ ምላሽ ሰጥተውኛል ብለዋል።
ጎረቤቶቻቸው በተገኙበት ከተደረገው ፍተሻ በኋላ፤ ሶስት የመስከረም አበራ ረቂቅ ጽሁፎችን እና የእርሷን “ሳምሰንግ” ሞባይል እንደወሰዱ ባለቤቷ ገልጸዋል። ከፍተሻው መጠናቀቅ በኋላ በሁለት “ፒክ አፕ” ተሸከርካሪዎች የመጡት የጸጥታ አካላት፤ “ለጥያቄ ስለምንፈልግሽ በቁጥጥር ስር ውለሻል” ብለው እንደወሰዷት ባለቤቷ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።
ባለቤታቸው ወዴት እንደምትወስድ ጥያቄ ሲያቀርቡ፤ የፈለጋት “የአዲስ አበባ ፖሊስ ነው” የምል ምላሽ ማግኘታቸውን አቶ ፍጹም አክለዋል። መስከረም የምትወሰድበትን ለማረጋገጥ ከጸጥታ አካላቱ ጋር አብረው መጓዛቸውን የሚናገሩት አቶ ፍጹም፤ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት በሚገኘው ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ሲያስረክቧት መመልከታቸውን አብራርተዋል።
መስከረም በባለቤትነት የምታስተዳድረው “ኢትዮ ንቃት” የዩቲዩብ መገናኛ ብዙሃን፤ ከሶስት ወራት ስራ ማቋረጥ በኋላ እንደገና ከተከታታዮቹ ጋር ለመገናኘት የበቃው ባለፈው መጋቢት 23፤ 2015 ነበር።
ለመገናኛ ብዙሃኑ ስራ መስተጓጎል፤ የመስከረም እስር በምክንያትነት ተጠቅሷል። ባለፈው ታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ በቁጥጥር ስር ውላ የነበረችው መስከረም፤ “ጥላቻ፣ አመጽ፣ ሁከትና ግጭት በመቀስቀስ” በፌደራል ዐቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶባታል። በዚያኑ ወር መጨረሻ፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የ50 ሺህ ብር በዋስትና በማስያዝ ጉዳይዋን በውጭ ሆና እንድትከታትል ውሳኔ በማስተላለፉ ከእስር ተፈትታለች።
መስከረም አበራ ለመጀመሪያ ጊዜ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለችው፤ ከአስራ አንድ ወራት ገደማ በፊት በግንቦት 2014 ዓ.ም ነበር። ፖሊስ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዋን የያዘው “ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት” ጠርጥሮ መሆኑን በወቅቱ ማስታወቁ አይዘነጋም። በዚህ ወቅት ለ25 ቀናት ያህል በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት በእስር ላይ የቆየችው መስከረም፤ ምንም አይነት ክስ ሳይመሰረትባት በ30 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር ተለቅቃለች።
(ዘገባው ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

10/04/2023

በጉራጌ ዞን የስራ ማቆም አድማ በማድረጋቸው ከ40 በላይ የንግድ ድርጅቶች መታሸጋቸው ታወቀ....
በጉራጌ ዞን የስራ ማቆም አድማ በማድረጋቸው ከ40 በላይ የንግድ ድርጅቶች መታሸጋቸው ታወቀ
“ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቀባበል አላደረጋችሁም በሚል ምክንያት እርምጃው እንደተወሰደበና በቀጣይ ሳምንትም በሌሎች ላይም ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወሰድ የንግድ ቢሮ ሰዎች ነግረውኛል” ሲል
በወልቂጤ ከተማ ሆቴሉ የተዘጋበት አንድ ነጋዴ ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል::
በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ እና ጉብርየ ተብሎ በሚጠሩ ቦታዎች ላይ ለ4ኛ ጊዜ ተደርጓል በተባለዉ የስራ ማቆም አድማ ላይ "ያለአግባብ" የንግድ ድርጅቶቻቸዉን ዘግተዋል የተባሉት ከ40 በላይ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን የከተማዉ የንግድና ልማት ቢሮ ማሸጉ ተነገረ።
ጠቅላይ ሚኒስተር ዐብይ አህመድ ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ከፌደራል እና ከክልል ርዕሰ መስተዳድራን እንዲሁም ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ወልቂጤ ከተማ መሄዳቸዉን ተከትሎ በዕለቱ የስራ ማቆም አድማ መደረጉ ይታወሳል።
ለአራተኛ ጊዜ በተደረገዉ የስራ ማቆም አድማ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጉራጌ የክልልነት ጥያቄን አስመልክቶ በፅህፈት ቤታቸዉ ሐሙስ መጋቢት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ከጉራጌ ተወላጅ ባለሀብቶች እና ምሁራን ጋር አድርገዉታል በተባለዉ ዉይይት "የክልልነት ጥያቄዉን ምላሽ መስጠት ከተፈለገ የደቂቃዎች ስራ ነዉ ነገር ግን ህዝብ የክላስተር መዋቅርን መቀበል አለበት በማለታቸው” ምክንያት አድማዉ መደረጉን የሚናገሩት መረጃ ሰጪዎቻችን "በዚሁ ተግባር ላይ ተሳትፋችኋል የተባሉ በአጠቃላይ 47 የንግድ ሱቆች ከመጋቢት 30 ጀምሮ እንዲታሸጉ መደረጉን" ተናግረዋል።
በመጀመሪያ ዙር እርምጃ ተወስዶባቸዋል በተባሉት በወልቂጤ ከተማ 30 እና በስሩ በሚገኘዉ ጉብርዬ ክፍለከተማ ደግሞ 17 የንግድ ድርጅቶች ላይ ሲሆን እስከ 50 ሺህ ብር ክፍያ ፈፅመዉ ወደ ስራቸዉ መመለስ እንደሚችሉ ነጋዴዎች ተነግሮናል ብለዋል።
(ዘገባው የአዲስ ዘይቤ ነው )

07/04/2023

በጎንደር፣ ባህር ዳር እና ወልዲያ ከተማዎች ባለው ውጥረት ምክንያት የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል
---
የፌደራል መንግስት “የየክልሉ ልዩ ኃይሎች ወደ ተለያዩ የፀጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ የሚያስችላቸውን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማካሄድ” መጀምሩን ከመግለፁ አስቀድሞ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ጉዳዩ ውጥረት ፈጥሯል።

በይፋ እንደተጀመረ የተገለፀው የክልል ልዩ ኃይልን በማፍረስ ወደ ሌሎች የፀጥታ መዋቅሮች የማስገባት እንቅስቃሴ ከመጋቢት 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በባህር ዳር፣ ጎንደር እና ወልዲያን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ውጥረት መፍጠሩን ምንጭዖች ገልጸዋል።

በዚህ ድርጊት የተነሳም በልዩ ኃይል አባላት እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት መካከል አለመግባባት መፈጠሩ በአካባቢዎቹ ለተከሰተው ውጥረት መንስዔ ሆኗል ።

በወልዲያ ከተማ ዙሪያ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ጎብየ ተብላ በምትጠራ ቦታ ላይ በልዩ ኃይል አባላትና በሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት መካከል ተኩስ ተከፍቶ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል ;;

ከትላንት ቀን ዘጠን ሰዓት ገደማ ጀምሮ በአካባቢው የተኩስ ልውውጥ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በወልዲያ እና አካባቢዋ የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጦ ይገኛል። በተመሳሳይ በጎንደር እና ባህር ዳር ከተማዎች ውስጥ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ የተደረገ ሲሆን በጎንደርና ባህርዳር ከተማ መካከል በምትገኘው ወረታ ከተማ እና በደብረታቦር ከተማ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀሩበት ሰዓት ድረስ ኢንተርኔት እየሰራ መሆኑ ታውቋል።

በቪፒኤን መተግብሪያዎች አማካኝነት ከአንድ ወር በላይ በከፊል ሲሰራ የቆየው የኢንተርኔት አገልግሎት መጋቢት 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በጎንደር፣ በባህርዳር እና በወልዲያ ከተማ አገልግሎቱን ሙሉ ለሙሉ ያቆመ ሲሆን በገመድ የተዘረጉ ዋይፋይ (ብሮድባንድ) ብቻ እየሰሩ መሆናቸውንም ማረጋገጥ ተችልዋል።
በሶስቱም ከተማዎች ከኢንተርኔት አገልግሎት ውጭ የስልክ እና የአጭር ፅሁፍ መልዕክቶች ክፍት ናቸው።
(ዘገባው የአዲስ ዘይቢ ነው)

07/04/2023

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ፍትሃዊ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ሊጠናከሩ ይገባል
----
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ፍትሃዊ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ሲሉ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አሳሰበ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር 8ኛው የውሃ ዲፕሎማሲ ተግባቦት ላይ ያተኮረ ፎረም እያካሄደ ነው።

በፎረሙ ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ ጭምሮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወካዮች እየተሳተፉ ነው።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞቿን ለመጠቀም ተፈጥሯዊ መብት ቢኖራትም በአንዳንድ የታችኛው ተፋሰስ አገራት በሃሰተኛ ትርክት እንቅፋት እየገጠማት ነው።
በውጭ ጉዳይ አማካኝነት የውሃ ዲፕሎማሲ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው የዲፕሎማሲ ጥረቱ ውጤታማ እንዲሆን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ምሁራን ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመላክተዋል።
ውሃን በተመለከተ ጥናትና ምርምር ማድረግ፣ የተገኘውን ውጤት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማሳወቅ ከምሁራኑ የሚጠበቅ መሆኑንም አንስተዋል።
በተለይም አባይን በሚመለከት ኢትዮጵያ ላይ የተነዙ ሃሰተኛ ትርክቶችን መመከት ላይ ምሁራን የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
ውሃ ላይ ትኩረት አድርገው ከሚሰሩ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በጋራ ለመሥራትና ግንኙነትን ለማጠናከር ሥምምነት ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አክለው ጠቁመዋል።
(ዘገባው የኢዚአ ነው)

07/04/2023

ከአዋሽ ወደ ወለንጪቲ ከተማ ሲጓዙ የነበሩ 15 አሽከርካሪዎች በታጣቂዎች መታገታቸውን ተሰማ
----
በኦሮሚያ ክልል ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ከአዋሽ ወደ ወለንጪቲ ከተማ ሲጓዙ የነበሩ 15 አሽከርካሪዎች በታጣቂዎች መታገታቸውን እና አምስቱ በተስኋላ መለቀቃቸውን የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን አስታወቀ። የቀሩትን አሽከርካሪዎች ለማስለቀቅ የጸጥታ አካላት “ኦፕሬሽን” መጀመራቸውን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ገልጿል።
የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃኔ ዘሩ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደገለጹት፤ አሽከርካሪዎቹ ባልታወቁ ታጣቂዎች የታገቱት ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ መጋቢት 26፤ 2015 በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ ውስጥ በምትገኘው ወለንጪቲ ከተማ አቅራቢያ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ በ117 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ወለንጪቲ ከተማ አቅራቢያ የታገቱት አሽከርካሪዎች፤ ማዳበሪያ እና ስኳር እያጓጓዙ እንደነበር የጠቆሙት አቶ ብርሃኔ፤ “የተወሰነው” ጭነት በታጣቂዎቹ መዘረፉን ተናግረዋል።
ታጣቂዎቹ አሽከርካሪዎቹን ወዳልታወቀ ቦታ መውሰዳቸውን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ ተሽከርካሪዎቹ ከእገታው በኋላም በቦታው ቆመው መቆየታቸውን አስረድተዋል። በአሽከርካሪዎቹ ላይ እገታ መፈጸሙን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያረጋገጡት የኢትዮጵያ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር አስተባባሪ አቶ አብዱራሂም መሀመድ፤ ተሽከርካሪዎቹ ዛሬ ከእገታው ቦታ መነሳታቸውን ተናግረዋል፡፡
የተሽከርካሪዎቹ ባለንብረቶች የባለቤትነት ማረጋገጫቸውን በማሳየት ከቦታው እንዲነሱ ማድረጋቸውንም አክለዋል፡፡ አቶ ብርሃኔ በበኩላቸው ከትላንት በስቲያ ከታገቱት ውስጥ አምስቱ የኦሮሚያ ክልል የመንግስት የልማት ድርጅት የሆነው ገዳ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ማህበር አሽከርካሪዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ እነዚህ አሽርካሪዎች ከቆይታ በኋላ መለቀቃቸውን፤ ይሁንና በምን አይነት መንገድ እንደተለቀቁ እስከአሁን መረጃ እንዳላገኙ አክለዋል።
የትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን የታገቱትን አሽከርካሪዎች ጉዳይ ለትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በማሳወቅ መፍትሄ እንዲፈለግ ጥያቄ ማቅረቡን አቶ ብርሃኔ ጨምረው ገልጸዋል። የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ደንጌ ቦሩ፤ የአሽከርካሪዎቹ ጉዳይ ወደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መድረሱን እና ከፌዴሬሽኑ አመራሮች ጋር ንግግር እየተደረገበት እንደሚገኝ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል፡፡
ሚኒስትር ዲኤታው ምን ያህል ተሽከርካሪዎች በታጣቂዎች እንደታገቱ ከመግለጽ ተቆጥበዋል። ከትላንት በስቲያ በአሽከርካሪዎቹ ላይ የተፈጸመው እገታ “የጸጥታ ችግር ሲኖር የሚከሰት” መሆኑን የገለጹት አቶ ደንጌ፤ “ከዚህ በፊትም እንደዚህ አይነት ችግሮች ነበሩ” ሲሉ ይህ አይነቱ ጥቃት ሲፈጸም የመጀመሪያ አለመሆኑን አመልክተዋል፡፡
የአሽከርካሪዎች እገታ የተፈጸመበት የኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ማንነታቸው ያልታቀወቁ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈጽሙበት ቆይተዋል፡፡ በተለይም በዚህ ዞን ውስጥ በምትገኘው መተሐራ ከተማ እና አከባቢው፤ ከዚህ ቀደም በታጣቂዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች የነዋሪዎች መገደላቸው አይዘነጋም፡፡ በወለንጭቲ አቅራቢያ የታገቱትን አሽከርካሪዎችን በተመለከተ የጸጥታ አካላት አካላት በአካባቢው “ኦፕሬሽን” መጀመራቸውን የተናገሩት የትራንስፖርት እና ሎጂቲክስ ሚኒስትር ዲኤታ “መንግስት [ጉዳዩን] እየተከታተለ ነው” ብለዋል፡፡ (ዘገባው የኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Address

Haile Gebresilase Street, Golagol Building
Addis Ababa
1000

Opening Hours

Monday 09:00 - 17:00
Tuesday 09:00 - 17:00
Wednesday 09:00 - 17:00
Thursday 09:00 - 17:00
Friday 09:00 - 17:00
Saturday 09:00 - 17:00

Telephone

+251983802752

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Mensh Media posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Business

Send a message to Mensh Media:

Share